ኤርምያስ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በይሁዳ ሕዝብ ላይ ስለሚደርሰው ፍርድ 1 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም፥ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አያዘነብልም፤ እነዚህን ሕዝቦች ከፊቴ አባርራቸው፤ ይውጡ። 2 እነርሱም፦ ወዴት እንሂድ ቢሉህ፥ አንተ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሞት የሆነ ወደ ሞት፥ ለሰይፍም የሆነ ወደ ሰይፍ፥ ለራብም የሆነ ወደ ራብ፥ ለምርኮም የሆነ ወደ ምርኮ ትላቸዋለህ። 3 ሰይፍን ለመግደል፥ ውሾችንም ለመጐተት፥ የሰማያትንም ወፎች፥ የምድርንም አራዊት ለመብላትና ለማጥፋት፥ አራቱን ዓይነት ጥፋት አዝዝባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 4 የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስለ አደረገው ሁሉ በምድር መንግሥታት ሁሉ መካከል ለመከራ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 5 “ኢየሩሳሌም ሆይ! የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ይጠይቅ ዘንድ ፈቀቅ የሚል ማን ነው? 6 አንቺ እኔን ከድተሽኛል፤ እኔንም መከተል ትተሻል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጠፋሻለሁ፤ ይቅርም አልላቸውም። 7 ሕዝቤንም ወደ ዳርቻ ፈጽሜ እበትናቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፤ ሕዝቤንም ስለ ኀጢአታቸው አጥፍቻቸዋለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም። 8 መበለቶቻቸውም ከባሕር አሸዋ ይልቅ በዝተዋል፤ በብላቴኖች እናት ላይ በቀትር ጊዜ አጥፊውን አምጥቻለሁ፤ ጭንቀትንና ድንጋጤን በድንገት አምጥቼባታለሁ። 9 ሰባት የወለደች ባዶ ቀረች፤ ነፍስዋም ተጨንቃለች፤ በቀትር ጊዜ ፀሐይዋ ገብታባታለች፤ አፍራለች፤ ተዋርዳማለች፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። ኤርምያስ ኀዘኑን እንደ ገለጠ 10 እናቴ ሆይ! ለምድር ሁሉ የክርክርና የጥል ሰው የሆንሁትን እኔን ወልደሽኛልና ወዮልኝ! ለማንም አልጠቀምሁም፤ ማንም እኔን አልጠቀመኝም፤ ከሚረግሙኝም የተነሣ ኀይሌ አለቀ። 11 አቤቱ! በመከራቸውና በጭንቃቸው ጊዜ በጠላቶቻቸው ዘንድ ስለ እነርሱ በጎ ነገር በአንተ ፊት የቆምሁ ባልሆን ይህ ለእነርሱ መከናወን ይሁን። 12 በውኑ ብረትን፥ የሰሜንን ብረት፥ ናስንም የሚሰብር አለን? 13 በዳርቻህ ሁሉ ስላለ ኀጢአትህ ሁሉ ፋንታ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለመበዝበዝ በከንቱ እሰጣለሁ። 14 እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እናንተንም ታቃጥላችኋለችና በማታውቀው ሀገር ለጠላቶችህ አስገዛሃለሁ። 15 አቤቱ! አንተ ታውቃለህ፤ አስበኝ፤ ጐብኘኝም፤ ከሚያሳድዱኝም አድነኝ እንጂ፥ አትታገሣቸው፤ ስለ አንተ እንደ ሰደቡኝ አስብ። 16 ቃልህ ተገኝቶአል፤ እኔም በልችዋለሁ፤ አቤቱ! የሠራዊት አምላክ ሆይ! ቃልህን የከዱ ሰዎችን አጥፋቸው፤ ስምህ በእኔ ላይ ተጠርትዋልና፥ ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። 17 በዋዘኞች ጉባኤ አልተቀመጥሁም፤ ነገር ግን በእጅህ ፊት ፈርቻለሁ፤ ምሬትን ሞልተህብኛልና ለብቻዬ ተቀመጥሁ። 18 የሚያሳዝኑኝ በእኔ ላይ ለምን ይበረታሉ? ቍስሌስ ስለ ምን የማይፈወስ ሆነ? ስለ ምንስ አልሽርም አለ? እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፥ እንዳልታመነች ውኃም ሆነብኝ። 19 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብትመለስ እመልስሃለሁ፤ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፤ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። 20 ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል፤ እኔ ግን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም። 21 ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፤ ከጨካኞችም ጡጫ እቤዥሃለሁ። |