ኤርምያስ 30:8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፤ እስራትህንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ለሌላ አትገዛም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ ‘በዚያ ቀን’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘በጫንቃቸው ላይ ያለውን ቀንበር እሰብራለሁ፤ እስራታቸውንም እበጥሳለሁ፤ ከእንግዲህ ባዕዳን አይገዟቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ባዕዳን አገልጋይ አያደርጉህም፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “ያ ቀን በደረሰ ጊዜ በሕዝቤ ጫንቃ ላይ የተጫነውን የአገዛዝ ቀንበር እሰብራለሁ፤ ሰንሰለታቸውንም አስወግዳለሁ፤ ከዚያን በኋላ ለባዕዳን ሕዝብ ባሪያዎች አይሆኑም፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለሌላ አትገዛም፥ |
እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፤ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፤ በሀገራቸውም ያርፋሉ፤ መጻተኞችም ከእነርሱ ጋር አንድ ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጨመራሉ።
አሦርን በምድሬ ላይ እሰብረዋለሁ፤ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፤ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሣል፤ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል።”
በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ፥ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል።
በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ በላያቸው የነበረው ቀንበር ተነሥቶአልና፥ በጫንቃቸው የነበረውንም፥ የአስጨናቂዎችንም በትር መልሶአልና።
ከጥንት ጀምሬ ቀንበርሽን ሰብሬአለሁ፤ እስራትሽንም ቈርጫለሁ፤ አንቺም፦ አላገለግልም አልሽ፤ ነገር ግን ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ ላይ፤ ከለምለምም ዛፍ ሁሉ በታች ለማመንዘር ተጋደምሽ።
ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አደራረጋቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።”
የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ለእርሱ ይገዙለታል።
“ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፤ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ።
ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።”
የግብፅን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል፤ የኀይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፤ ደመናም ይጋርዳታል፤ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ።
የምድረ በዳ ዛፍም ፍሬውን ይሰጣል፤ ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፤ በምድራቸውም በሰላም ታምነው ይኖራሉ፤ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ፥ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።