ኢሳይያስ 61:6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፤ የአምላካችንም አገልጋዮች ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፤ በሀብታቸውም ትመካላችሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤ የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናንተ ግን የጌታ ካህናት ትባላላችሁ፤ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፤ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በሀብታቸውም ትከብራላችሁ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንተ ግን “የእግዚአብሔር ካህናትና የአምላካችን አገልጋዮች” ተብላችሁ ትጠራላችሁ። በሕዝቦች ሀብት ትደሰታላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትከብራላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናንተ ግን የእግዚአብሔር ካህናት ትባላላችሁ፥ ሰዎቹም የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሩአችኋል፥ የአሕዛብን ሀብት ትበላላችሁ፥ በክብራቸውም ትመካላችሁ። |
ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ለመብላትና ለመጠጣት፥ ለመጥገብም፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመታሰቢያ ይሆናል እንጂ ለእነርሱ አይሰበሰብም።
እንደ ገናምበቀኝና በግራ ተስፋፊ፤ ዘርሽ አሕዛብን ይወርሳሉና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ታደርጊያለሽና።
ከሌላም ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን ለእርሱም ባሪያዎች የሆኑትን፥ የእግዚአብሔርንም ስም የወደዱትን፥ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎቹ የሆኑትን፥ “ሰንበታቴን የሚጠብቁትንና የማያረክሱትን፥ በቃል ኪዳኔም ጸንተው የሚኖሩትን ሁሉ፥
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ልጆቻቸውንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል፤ በጕልበታቸውም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏቸዋል።
የሚቃጠለውንም መሥዋዕት የሚያቀርብ፥ የእህሉንም ቍርባን የሚያቃጥል፥ ሁልጊዜም የሚሠዋ ሰው ከሌዋውያን ካህናት ዘንድ በእኔ ፊት አይታጣም።”
ይኸውም የእስራኤል ቤት ደግሞ ከእኔ ርቀው እንዳይስቱ፥ በኀጢአታቸውም ሁሉ እንዳይረክሱ ነው፤ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው።
እንግዲህ ጳውሎስ ምንድን ነው? አጵሎስስ ምንድን ነው? እነርሱስ በቃላቸው የአመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ነው።
እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ቢሆኑም እኔም እንደ ሰነፍ ለራሴ እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ እጅግም ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ።
ነገር ግን በሁሉ ራሳችንን አቅንተን፥ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንሁን፤ በብዙ ትዕግሥትና በመከራ፥ በችግርና በጭንቀት ሁሉ፥
እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ።
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤
በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።