ዘፀአት 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል ወደ ሲና እንደ ደረሱ 1 የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በሦስተኛው ወር በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። 2 ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈሩ። 3 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ጠርቶ አለው፥ “ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ንገር፤ 4 በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ እንደ ንስር ክንፍም እንደ ተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። 5 አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ፥ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ። 6 እናንተም የክህነት መንግሥት፥ የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ ይህንም ቃል ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።” 7 ሙሴም መጣ፤ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ። 8 ሕዝቡም ሁሉ አንድ ቃል ሆነው፥ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እንሰማለን፤ እናደርጋለንም” ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ። 9 እግዚአብሔር ሙሴን፥ “ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘለዓለም እንዲያምኑብህ፥ እነሆ፥ በዐምደ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለእግዚአብሔር ነገረ። 10 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ውረድ፤ ዛሬና ነገ ራሳቸውን ያንጹ፤ ልብሳቸውንም ያጥቡ ዘንድ ሕዝቡን እዘዛቸው። 11 በሦስተኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጅተው ይጠብቁ። 12 ለሕዝቡም በዙሪያው ወሰን አድርግላቸው፤ ወደ ተራራው እንዳትወጡ፥ ከእርሱ ማንኛውንም ክፍል እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል” ብለህ ንገራቸው፤ 13 የማንም እጅ አይንካ፤ የሚነካውም ሁሉ በድንጋይ ይወገራል፤ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳ ወይም ሰው ቢሆን የቀረበ አይድንም። የመለከት ድምፅና ደመና በተራራው በዐለፈ ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ። 14 ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፤ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ። 15 ሕዝቡንም፥ “ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፤ ወደ ሴቶቻችሁም አትቅረቡ” አለ። 16 እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ፥ ከባድም ደመና፥ ጉምም በሲና ተራራ ላይ ሆነ፤ እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምፅ ተሰማ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። 17 ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ በተራራውም እግርጌ ቆሙ። 18 እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ እንደ ምድጃ ጢስ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፤ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር፤ ሕዝቡም ፈጽመው ደነገጡ። 19 የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ እየፈጠነ በርትቶ ይሰማ ነበር። ሙሴም ተናገረ፤ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት። 20 እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ። 21 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ውረድ፤ ይህንም ለመረዳት ወደ እግዚአብሔር እንዳይቀርቡ፥ ከእነርሱም ብዙ እንዳይጠፉ ለሕዝቡ አስጠንቅቃቸው፤ 22 ወደ እግዚአብሔርም የሚቀርቡት ካህናት ደግሞ እንዳያጠፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ” አለው። 23 ሙሴም እግዚአብሔርን፥ “ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ይወጡ ዘንድ አይችሉም፤ አንተ፦ በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸኛልና” አለው። 24 እግዚአብሔርም፥ “ሂድ፤ ውረድ፤ አንተ አሮንም ከአንተ ጋር ትወጣላችሁ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጡ ዘንድ አይደፋፈሩ” አለው። 25 ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደ፤ ይህንም ነገራቸው። |