ኢሳይያስ 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት። የኬልቀዶን መርከቦች ሆይ፥ አልቅሱ፤ ጠፍተዋልና፤ እንግዲህም ከኬጤዎን ሀገር አይመጡምና ማርከውም ይወስዱአቸዋልና። 2 በደሴት የሚኖሩ በባሕር የሚሻገሩ የፊኒቄ ስደተኞች ምን ይመስላሉ? 3 የገቡ ስደተኞች አሕዛብ በመከር ጊዜ እንደሚለወጥ ዘር ናቸው። 4 ሲዶና ሆይ፥ ባሕር፥ የባሕር ምሽግ፥ “አላማጥሁም፥ አልወለድሁም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፥ ደናግልንም አላሳደግሁም” ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ። 5 ወሬዋ ወደ ግብፅ በደረሰ ጊዜ ስለ ጢሮስ ምጥ ይይዛቸዋል። 6 ወደ ኬልቄዶን ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ፥ አልቅሱ። 7 ተማርካችሁ ሂዱ እንጂ ይህች ዕረፍት የእናንተ አይደለችም። 8 በጢሮስ ላይ ይህን የመከረ ማን ነው? እርስዋ ከሁሉ የምትሻልና የምትበልጥ አይደለችምን? ነጋዴዎችዋ የከበሩ የምድር አለቆች ናቸው። 9 የክቡራንን ትዕቢት ይሽር ዘንድ፥ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያዋርድ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል። 10 ምድርህን እረስ፤ እንግዲህ መርከቦች ከኬልቀዶን አይመጡምና። 11 ነገሥታቱን ያበሳጨቻቸው የባሕር ሰዎች እጃቸው ትደክማለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም የከነዓንን ኀይል ያጠፉ ዘንድ አዘዘ። 12 እርሱም፥ “አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፤ በዚያም ደግሞ አታርፊም” አለ። 13 እነሆ፥ የከለዳውያንን ሀገር አሦራውያን አጥፍተዋታልና፤ ግንብዋም ወድቆአል፤ 14 እናንተ የኬልቀዶን መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ። 15 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ወይም እንደ አንድ ሰው ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። 16 አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ፤ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ፤ ዘፈንሽንም አብዢ። 17 ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን በይቅርታ ይጐበኛታል፤ ወደ ጥንቷም ትመለሳለች፤ ደግሞም ለዓለም መንግሥታት ሁሉ መናገሻና መናገጃ ትሆናለች። 18 ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ለመብላትና ለመጠጣት፥ ለመጥገብም፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመታሰቢያ ይሆናል እንጂ ለእነርሱ አይሰበሰብም። |