2 ቆሮንቶስ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለእግዚአብሔር ስለሚደረግ ቅንዐት 1 በስንፍናዬ እናገር ዘንድ ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤ ቢሆንም በርግጥ ታገሡኝ፤ 2 ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና። 3 ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ከክርስቶስ የዋህነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 4 ወደ እናንተ የመጣና እኛ ወደ አላስተማርናችሁ ወደ ሌላ ኢየሱስ የጠራችሁ ቢኖር፥ ወይም ያልተቀበላችሁት ሌላ መንፈስ ቢኖር፥ ወይም ያልተማራችሁት ሌላ ወንጌል ቢኖር ልትጠብቁን ይገባል። 5 እኔ ግን ሌሎች ሐዋርያት ከአስተማሩት ያጐደልሁባችሁ የለም ይመስለኛል። ወንጌልን ያለ ዋጋ ስለ ማስተማር 6 እኔ በአነጋገሬ አላዋቂ ብሆንም በዕውቀት ግን እንዲሁ አይደለሁም፤ ነገር ግን ሁሉን በሁሉ እገልጥላችኋለሁ። 7 ወይስ ራሴን በሁሉ ያዋረድሁ በደልሁ ይሆን? እናንተ ከፍ ከፍ ትሉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ዋጋ አስተምሬአችኋለሁና። 8 እናንተን አገለግል ዘንድ፥ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተቀብዬ፥ ለምግቤ ያህል ወሰድሁ፤ 9 ከእናንተ ዘንድ በነበርሁበት ጊዜም፥ ስቸገር ገንዘባችሁን አልተመኘሁም። ባልበቃኝም ጊዜ ወንድሞቻችን ከመቄዶንያ መጥተው አሙአሉልኝ፤ በእናንተም ላይ እንዳልከብድባችሁ በሁሉ ተጠነቀቅሁ፤ ወደ ፊትም እጠነቀቃለሁ። 10 የክርስቶስ ዕውነት አብሮኝ ይኖራልና፥ ይህቺ ደስታዬ በአካይያ አውራጃ አልተከለከለችብኝም። 11 ስለምን ነው? አልወዳችሁምና ነውን? እንደምወድዳችሁስ እግዚአብሔር ያውቃል። 12 ነገር ግን ያደረግሁትም ቢሆን፥ የማደርገውም ቢሆን፥ እነርሱ እንደ እኛ የሚመኩበትን ያገኙ ዘንድ፥ ምክንያት የሚሹትን ምክንያት አሳጣቸው ዘንድ ነው። 13 የሚተነኰሉ፥ ራሳቸውን የክርስቶስን ሐዋርያት የሚያስመስሉ፥ ዐመፅንም የሚያደርጉ ሐሰተኞች ሐዋርያት አሉና። 14 ይህም አያስደንቅም፤ ሰይጣን ራሱ ተለውጦ እንደ ብርሃን መልአክ ይመስላልና። 15 መልእክተኞቹም የጽድቅ መላእክትን ቢመስሉ፥ ይህ ታላቅ ነገር አይደለም፤ ፍጻሜያቸው ግን እንደ ሥራቸው ነው። ስለ መንፈሳዊ ትምክሕት 16 ደግሞም እንዲህ እላለሁ፦ ሰነፍ የሚያደርገኝ አይኑር፤ ያውም ብሆን እኔ ጥቂት እመካ ዘንድ እንደ ሰነፍ እንኳ ብሆን ተቀበሉኝ። 17 ይህም ቢሆን የምናገረው ለእግዚአብሔር የሚገባ አይደለም፤ ነገር ግን ስለዚህች ትምክሕቴ እንደ ሰነፍ እናገራለሁ። 18 በሥጋዊ ሥርዐት የሚመኩ ብዙዎች ናቸውና እኔ ደግሞ እመካለሁ። 19 እናንተ ልባሞች ስትሆኑ ሰነፎችን መስማት ደስ ያሰኛችኋልና። 20 የሚገዙአችሁንና የሚቀሙአችሁን፥ መባያ የሚያደርጓችሁንና የሚታበዩባችሁን፥ ፊታችሁንም በጥፊ የሚመትዋችሁን ትታገሡአቸዋላችሁና። 21 እኛ እንደ ደካሞች መስለን እንደ ነበርን፥ ይህን በውርደት እናገራለሁ፤ ነገር ግን ማንም በሚደፍርበት እኔ ደግሞ እደፍራለሁ። 22 እነርሱ ዕብራውያን ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ፤ እነርሱ እስራኤላውያን ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ፤ እነርሱ የአብርሃም ልጆች ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ነኝ። 23 እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ቢሆኑም እኔም እንደ ሰነፍ ለራሴ እናገራለሁ፤ እኔ እበልጣለሁ፤ እጅግም ደከምሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገረፍሁ፤ ብዙ ጊዜም ታሰርሁ፤ ብዙ ጊዜም ለሞት ተዘጋጀሁ። 24 አይሁድ አንዲት ስትቀር አምስት ጊዜ አርባ አርባ ገረፉኝ። 25 ሦስት ጊዜ በበትር ደበደቡኝ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ መቱኝ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረች፤ በጥልቁ ባሕር ውስጥ ስዋኝ አድሬ፥ ስዋኝ ዋልሁ። 26 በመንገድ ዘወትር መከራ እቀበል ነበር፤ በወንዝም መከራ ተቀበልሁ፤ ወንበዴዎችም አሠቃዩኝ፤ ዘመዶችም አስጨነቁኝ፤ አሕዛብ መከራ አጸኑብኝ፤ በከተማ መከራ ተቀበልሁ፤ በበረሃም መከራ ተቀበልሁ፤ በባሕርም መከራ ተቀበልሁ፤ ሐሰተኞች መምህራን መከራ አጸኑብኝ። 27 በድካምና በጥረት፥ ብዙ ጊዜም ዕንቅልፍ በማጣት፥ በመራብና በመጠማት፥ አብዝቶም በመጾም፥ በብርድና በመራቆት ተቸገርሁ። 28 የቀረውንም ነገር ሳልቈጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። 29 ታሞ እኔ የማላዝንለት ማን ነው? በድሎስ እኔ የማልደነግጥለት ማን ነው? 30 መመካት የሚገባ ከሆነስ እኔም በመከራዬ እመካለሁ። 31 ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ሐሰት እንደማልናገር ያውቃል። 32 በደማስቆ ከተማ ከንጉሥ አርስጣስዮስ በታች የሆነ የአሕዛብ አለቃ ሊይዘኝ ወድዶ የደማስቆን ከተማ ያስጠብቅ ነበር። 33 በቅርጫትም አድርገው በመስኮቱ በኩል በአጥሩ ላይ አወረዱኝ፤ ከእጁም አመለጥሁ። |