ኢሳይያስ 52:8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነሆ፥ የሚጠብቁሽ ሰዎች ድምፅ ከፍ ከፍ ይላልና፥ እግዚአብሔርም ጽዮንን ይቅር ባላት ጊዜ ዐይን በዐይን ይተያያሉና በአንድነት በቃላቸው ደስ ይላቸዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስሚ! ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገዋል፤ በአንድነት በእልልታ ይዘምራሉ። እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስ፣ በዐይኖቻቸው ያያሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነሆ፥ ጉበኞችሽ ጮኸዋል፤ ጌታ ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዐይን በዐይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር ወደ ጽዮን ሲመለስ በግልጽ ስለሚያዩ ከተማ ጠባቂዎችሽ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የደስታ መዝሙር ሲዘምሩ አድምጪ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነሆ፥ ጕበኞችሽ ጮኸዋል፥ እግዚአብሔር ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዓይን በዓይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ። |
ከተማዪቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፤ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፤ ቅጥር ጠባቂዎችም የዐይነ ርግብ መሸፈኛዬን ከራሴ ላይ ወሰዱት።
እነዚህ ድምፃቸውን ያነሣሉ፤ በምድር የቀሩትም ስለ እግዚአብሔር ክብር በአንድነት ደስ ይላቸዋል፤ የባሕርም ውኃ ይናወጣል።
በዚያም ቀን ይህን ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘምራሉ፤ እነሆም፥ የጸናችና የምታድን፥ ቅጥርንና ምሽግንም የምታደርግ ከተማ አለችን።
እግዚአብሔርም የሕዝቡን ስብራት በጠገነ ዕለት፥ በመቅሠፍቱ የቈሰለውንም በፈወሰ ዕለት፥ የጨረቃ ብርሃን እንደ ፀሐይ ብርሃን፥ የፀሐይም ብርሃን እንደ ሰባት ቀን ብርሃን ሰባት እጥፍ ይሆናል።
በእግዚአብሔር የተሰበሰቡም ይመለሳሉ፤ በደስታም ተመልሰው ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘለዓለም ደስታም በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታንም ያገኛሉ፤ መከራ፥ ኀዘንና ትካዜም ይጠፋሉ።
ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ ለኢየሩሳሌም የምሥራችን የምትነግር ሆይ፥ ድምፅህን በኀይል አንሣ፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለህ ንገር።
ከባቢሎን ውጡ፤ ከከለዳውያንም ኰብልሉ፤ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፤ ይህም ይሰማ፤ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ አውሩና፥ “እግዚአብሔር ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል” በሉ።
ሁሉም ዕውራን እንደ ሆኑ ኑና እዩ፤ ሁሉ ያለ ዕውቀት ናቸው፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው፤ ይጮኹም ዘንድ አይችሉም፤ በመኝታቸውም ሕልምን ያልማሉ፤ ማንቀላፋትንም ይወድዳሉ።
በኀይልህ ጩኽ፤ አትቈጥብ፤ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፤ ለሕዝቤ ኀጢአታቸውን፥ ለያዕቆብ ቤትም በደላቸውን ንገር።
ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጠባቂዎችሽን በቅጥርሽ ላይ ቀንና ሌሊት አቁሜአለሁ፤ እግዚአብሔርን የሚያስቡ ከቶ ዝም አይሉም፤
ይመጣሉ፤ በጽዮንም ተራራ ደስ ይላቸዋል፤ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ፥ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ሀገርም ይሰበሰባሉ፤ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይራቡም።
ለእነርሱም፥ ከእነርሱም በኋላ ለልጆቻቸው መልካም ይሆንላቸው ዘንድ ለዘለዓለም እንዲፈሩኝ ሌላ መንገድና ሌላ ልብ እሰጣቸዋለሁ።
የሐሤት ድምፅና የደስታ ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራ ድምፅና የሴት ሙሽራ ድምፅ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና፥ ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ የሚሉ ሰዎች ድምፅ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የምስጋናን መሥዋዕት የሚያመጡ ሰዎች ድምፅ እንደ ገና ይሰማል። የዚያችን ምድር ምርኮኞች ቀድሞ እንደ ነበረ አድርጌ እመልሳለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር።
በዚያ ቀን እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ይመክትላቸዋል፣ በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት ይሆናል፣ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ አምላክ ይሆናል።
ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ “ይህ የእኔ ገንዘብ ነው” የሚል አልነበረም።
ወንድሞቻችን! አንድ ቃል እንድትናገሩ፥ እንዳታዝኑ፥ ፍጹማንም እንድትሆኑ፥ ሁላችሁንም፦ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ አሳብ ሆናችሁ ኑሩ።
አሁን ግን ታወቀኝ፤ በግልጥም ተረዳኝ፤ በመስታወትም እንደሚያይ ሰው ዛሬ በድንግዝግዝታ እናያለን፤ ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ አሁን በከፊል፥ ኋላ ግን እንደ ተገለጠልኝ መጠን ሁሉን አውቃለሁ።
ለመምህሮቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም፤ ስለ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ምላሽ የሚሰጡ እንደ መሆናቸው፥ ይህን ሳያዝኑ ደስ ብሎአቸው ያደርጉት ዘንድ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉና።