ዕብራውያን 9:15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስለዚህ ኢየሱስ ሞትን ተቀብሎ፥ በቀደመው ሥርዐት ስተው የነበሩትን ያድናቸው ዘንድ ወደ ዘለዓለም ርስቱም የጠራቸው ተስፋውን ያገኙ ዘንድ፥ ለአዲሲቱ ኪዳን መካከለኛ ሆነ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ስለዚህም የተጠሩት፣ ተስፋ የተሰጠውን የዘላለም ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፤ በመጀመሪያው ኪዳን ሥር በነበሩበት ጊዜ ከሠሩት ኀጢአት ነጻ ለማውጣት ቤዛ ሆኖ ሞቷልና። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚህ ምክንያት የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞቱ ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘለዓምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እነዚያ የተጠሩት እግዚአብሔር በተስፋ የሰጠውን ዘለዓለማዊ ርስት እንዲቀበሉ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ማእከላዊ አስማሚ ሆኖአል፤ ይህም የሆነው ሰዎችን በመጀመሪያው ቃል ኪዳን ሥር ሆነው ከሠሩት ኃጢአት ለማዳን እርሱ በመሞቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። |
ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።
እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና “ቸር መምህር ሆይ! የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ጠየቀው።
እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋዉን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈስሰው ደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።
አሁንም ለእግዚአብሔርና ሊያንጻችሁ፥ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ሊሰጣችሁ ለሚችለው ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።
እና የእግዚአብሔር ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር ካለን፥ ከታረቀን በኋላም በልጁ ሕይወት እንዴት የበለጠ ያድነን!
በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ሕግ አገልጋዮች አደረገን፤ ፊደል ይገድላል፥ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል።
በእስራቴም ጊዜ ከእኔ ጋር በመከራ ተባብራችኋል፤ የገንዘባችሁንም መዘረፍ በደስታ ተቀብላችኋል፤ በሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር ከዚህ የሚበልጥና የተሻለ ገንዘብ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና።
እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፤ ተስፋቸውንም አላገኙም፤ ነገር ግን ከሩቅ አይተው እጅ ነሱኣት፤ በምድሪቱም ላይ እነርሱ እንግዶችና መጻተኞች እንደ ሆኑ ዐወቁ።
የአዲስ ኪዳንም መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ ተረጨው ደሙ ደርሳችኋል።
ልጆች በሥጋና በደም አንድ ናቸውና፤ እርሱ ደግሞ በዚህ ከእነርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ ለእነርሱም እንደ ወንድም ሆነላቸው፤ መልአከ ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ፥ ይኸውም ሰይጣን ነው።
አሁንም ከሰማያዊ ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞቻችን ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ።
እንዲሁ ክርስቶስም የብዙዎችን ኀጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ራሱን አንድ ጊዜ ሠዋ፤ በኋላ ግን ያድናቸው ዘንድ ተስፋ ለሚያደርጉት ያለ ኀጢአት ይገለጥላቸዋል።
ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዐመፀኞች አንድ ጊዜ በኀጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችሁማል፤ ያበረታችሁማል።
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል ታርደሃልና፤ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ፥ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ፤” እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።