ዕብራውያን 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለሚመጣው ዓለም 1 ስለዚህም ከሰማነው ነገር ምንአልባት እንዳንወሰድ ለእርሱ አብዝተን ልንጠነቀቅ ይገባናል። 2 በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ 3 እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበረና የሰሙትም ለእኛ አጸኑት። 4 እግዚአብሔርም እንደ ራሱ ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በመስጠት፥ በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በልዩ ልዩ ተአምራትም መሰከረላቸው፤ ነገራቸውንም አስረዳላቸው። 5 ስለ እርሱ የምንናገርለትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛ አይደለም። 6 ነገር ግን መጽሐፍ እንዲህ ብሎ የመሰከረበት ስፍራ አለ፤ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጐበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? 7 ከመላእክትህ ጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድንም ጫንህለት፤ በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው። 8 ሁሉንም ከእግሩ በታች አድርገህ አስገዛህለት።” ሁሉን ለእርሱ ባስገዛለት ጊዜም የተወውና ያላስገዛለት የለም፤ አሁን ግን ሁሉን እንዳስገዛለት አናይም። 9 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ጭኖ እናየዋለን። 10 ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእጁ ለተያዘ፥ በእርሱም ሁሉ ለሆነ ለእርሱ ተገብቶታልና። 11 እነርሱን የቀደሳቸው እርሱ፥ የተቀደሱት እነርሱም ሁሉም በአንድነት ከአንዱ ናቸውና። ስለዚህም እነርሱን፥ “ወንድሞች” ማለትን አያፍርም። 12 “ስምህን ለወንድሞች እነግራቸዋለሁ፤ በማኅበር መካከልም አመሰግንሃለሁ” አለ። 13 ዳግመኛም፥ “እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች እነሆ፥” አለ፤ ዳግመኛም፥ “እኔ እታመንበታለሁ” አለ። 14 ልጆች በሥጋና በደም አንድ ናቸውና፤ እርሱ ደግሞ በዚህ ከእነርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ ለእነርሱም እንደ ወንድም ሆነላቸው፤ መልአከ ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ፥ ይኸውም ሰይጣን ነው። 15 በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሞትን በመፍራት የተቀጡትን፥ ለባርነት የተገዙትንም ሁሉ ያሳርፋቸው ዘንድ። 16 የነሣውን ከአብርሃም ዘር እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምና። 17 ስለዚህም የሕዝብን ኀጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። 18 እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና። |