1 ተሰሎንቄ 4:16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤ ክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና። በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ራሱ በትእዛዝ ቃል በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፤ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የትእዛዝ ድምፅ፥ የመላእክት አለቃ ድምፅ፥ የእግዚአብሔር እምቢልታም ይሰማል፤ ጌታ ራሱም በእነዚህ ታጅቦ ከሰማይ ይወርዳል፤ በክርስቶስ አምነው የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ |
እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ፥ ከባድም ደመና፥ ጉምም በሲና ተራራ ላይ ሆነ፤ እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምፅ ተሰማ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።
ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው ርቀው ቆሙ።
በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦርም የጠፉ፥ በግብፅ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፤ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።
እግዚአብሔርም በሠራዊቱ ፊት ድምፁን ይሰጣል፤ ሰፈሩ እጅግ ብዙ ነውና፥ የቃሉም ሥራ ጽኑዕ ነውና፤ የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግ የምታስፈራ ናትና፥ ፈጽማ ትገለጣለች፥ መጠኗ ምንድን ነው? ማንስ ይችላታል?
ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፣ ሰዎችም፦ ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል ብሎ ተናገረኝ።
እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ይገለጣል፥ ፍላጻውም እንደ መብረቅ ይወጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም መለከትን ይነፋል፥ በደቡብም ዐውሎ ነፋስ ይሄዳል።
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፣ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፣ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫንይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
በያዕቆብ ላይ ድካም የለም፤ በእስራኤልም ሕማም አይታይም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፤ የአለቆችም ክብር ለእርሱ ነው።
ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤” አለው።
እነርሱም፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየአያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፥ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” አሏቸው።
ነገር ግን ሰው ሁሉ በየሥርዐቱ ይነሣል፤ በመጀመሪያ ከሙታን የተነሣ ክርስቶስ ነው፤ ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ያመኑ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ ይነሣሉ።
ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት “የጌታ ቀን ደርሶአል፤” ብላችሁ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።
የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፤ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።
የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር “ጌታ ይገሥጽህ!” አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ። “ይህንን ጻፍ፡ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።” መንፈስም “አዎን! ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል፤” ይላል።
አየሁም፤ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ “ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።