Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ራእይ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ሰባተኛው ማኅተምና የወርቁ ማዕጠንት

1 ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ግማሽ ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ።

2 በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው።

3 ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።

4 የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።

5 መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት፤ ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።


ሰባቱ መለከቶች

6 ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ።

7 ፊተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፤ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።

8 ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ፤

9 በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ።

10 ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞችና በውሃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ።

11 የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፤ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ።

12 አራተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፤ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።

13 አየሁም፤ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ “ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos