መዝሙር 47 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በሁለተኛ ሰንበት ማግሥት የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ በአምላካችን ከተማ በመቅደሱ ተራራ ምስጋናው ብዙ ነው። 2 ለምድር ሁሉ ደስታን የሚያዝዝ፥ የጽዮን ተራራዎች በመስዕ በኩል ናቸው። የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናት። 3 በተቀበሏት ጊዜ እግዚአብሔር በረከትዋን ያውቃል 4 እነሆ፥ የምድር ነገሥታት ተሰብስበው በአንድነት መጥተዋል። 5 እነርሱስ ይህን አይተው አደነቁ፥ ደነገጡ፥ ፈሩም። 6 መንቀጥቀጥም ያዛቸው፥ እንደ ወላድም በዚያ አማጡ። 7 በኀይለኛ ነፋስ የተርሴስን መርከቦች ትቀጠቅጣቸዋለህ። 8 እንደሰማን እንዲሁ አየን፥ በሠራዊት ጌታ ከተማ፥ በአምላካችን ከተማ፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም ያጸናታል። 9 አምላክ ሆይ፥ በአሕዛብ መካከል ይቅርታህን ተቀበልን። 10 አምላክ ሆይ፥ እንደ ስምህ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስጋናህ ነው። ቀኝህ ጽድቅን የተመላ ነው። 11 አቤቱ፥ ስለ ፍርድህ የጽዮን ተራሮች ደስ ይላቸዋል፥ የይሁዳም ሴቶች ልጆች ሐሤት ያደርጋሉ። 12 ጽዮንን ክበቡአት፥ ዕቀፉአትም። በቅጥሮችዋም ተናገሩ፤ 13 በብርታቷ ልባችሁን አኑሩ፤ በረከቷንም ትካፈላላችሁ ለሚመጣውም ትውልድ ትነግሩ ዘንድ። 14 ለዓለምና ለዘለዓለም ይህ አምላካችን እንደ ሆነ፥ እርሱም ለዘለዓለም ይጠብቀናል። |