ምሳሌ 3:1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ልጄ ሆይ! የማስተምርህን አትርሳ፤ ትእዛዞቼንም በልብህ ጠብቅ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ልጄ ሆይ! ሕጎቼን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። |
እነሆ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤
ሕዝቤ እኔን በሚገባ ካለማወቁ የተነሣ ጠፍቶአል፤ እናንተ እኔን ለማወቅ ስላልፈለጋችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንድታገለግሉኝ አልፈልጋችሁም፤ ሕጌንም ስላቃለላችሁና ስለ ረሳችሁ ልጆቻችሁ በእኔ ዘንድ የተረሱ ይሆናሉ።
ስለዚህ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ እርግጠኞች ሁኑ፤ ምንም ዐይነት የተቀረጸ ምስል እንዳትሠሩ፤ የነገራችሁንም ትእዛዝ ፈጽሙ።
እንግዲህ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይህን በዐይናችሁ ያያችሁትን ሁሉ እንዳትረሱና ከአእምሮአችሁ እንዳይጠፋ ተጠንቀቁ። ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁም አስተምሩአቸው፤
“ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ባዘዝኩህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ በምሰጥህ ምድር የረዥም ዘመን ዕድሜ ይኖርሃል።
“በሕይወት መኖር እንድትችሉ፥ ቊጥራችሁ እንዲበዛ፥ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁ ሊሰጣቸው ቃል የገባላቸውን ምድር ለመውረስ እንድትበቁ፥ ዛሬ እኔ የሰጠኋችሁን ትእዛዝ ሁሉ በታማኝነት ጠብቁ።