Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ምሳሌ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከጥበብ የሚገኝ ጥቅም

1 ልጆቼ ሆይ! የአባታችሁን ምክር ስሙ፤ በጥንቃቄ አዳምጡ፤ ማስተዋልንም ታገኛላችሁ።

2 እኔ የማስተምራችሁ ትምህርት መልካም ስለ ሆነ ቸል አትበሉት።

3 እኔም አንድ ጊዜ ከአባቴ ጋር የምኖር ትንሽ ልጅ ነበርኩ፤ ለእናቴም አንድ ነበርኩ፤

4 አባቴም እንዲህ እያለ ያስተምረኝ ነበር፤ “ቃሌን በሙሉ ልብህ ያዘው፤ ትእዛዞቼንም ፈጽም፤ በሕይወትም ትኖራለህ።

5 ጥበብንና ማስተዋልን ለማግኘት ትጋ፤ እኔ የምልህን አትርሳ፤ ቸልም አትበለው።

6 ጥበብን አትተዋት፤ እርስዋም ትጠብቅሃለች፤ ውደዳት፤ እርስዋም ከአደጋ ሁሉ ትከላከልልሃለች።

7 ጥበብ ከሁሉ በላይ ስለ ሆነች እርስዋን ገንዘብ አድርግ፤ ያለህን ሁሉ ቢያስከፍልህም ማስተዋልን ለማግኘት ትጋ።

8 ጥበብን አክብራት፤ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ አጥብቀህም ብትይዛት፥ ክብርን ትሰጥሃለች።

9 የክብርን አክሊል ታቀዳጅሃለች፤ የተዋበውንም ዘውድ ትሰጥሃለች።”

10 ልጄ ሆይ! አድምጠኝ፤ የምነግርህንም ስማ፤ ዕድሜህም ይረዝማል።

11 የጥበብን መንገድ አሳየሁህ፤ በቀና መንገድም መራሁህ።

12 በጥበብ ብትራመድ እርምጃህ አይታገድም፤ ብትሮጥም አትሰናከልም።

13 የተማርከው ትምህርት ሕይወትን ስለሚሰጥህ አጥብቀህ ያዘው፤ አትተወው፤ ደኅና አድርገህም ጠብቀው።

14 ክፉ ሰዎች በሚሄዱበት መንገድ አትሂድ፤ ምሳሌነታቸውንም አትከተል።

15 ከእርሱ ራቅ፤ በዚያም አትራመድ፤ ከእርሱ ርቀህ በራስህ መንገድ ሂድ።

16 ክፉ ነገር ካላደረጉ ዕረፍት አይኖራቸውም፤ በሰው ላይ ጒዳት ካላደረሱ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ።

17 ዐመፅና ግፍ ለእነርሱ እንደ መብልና እንደ መጠጥ ናቸው።

18 የደጋግ ሰዎች መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው፤ የቀኑ ሙሉ ብርሃን እስኪሆን ድረስ ብርሃኑ እየጨመረ ይሄዳል።

19 የክፉዎች መንገድ ግን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነው፤ ይወድቃሉ፤ የመውደቂያቸው ምክንያት ምን እንደ ሆነ አያውቁም።

20 ልጄ ሆይ! እኔ የምለውን አተኲረህ ስማ፤ ንግግሬንም በጥሞና አድምጥ።

21 ከዐይንህ አታርቃቸው፤ በልብህም ውስጥ ጠብቃቸው።

22 እነርሱም ለሚያስተውሉአቸው ሕይወትን፥ ለመላ ሰውነትም ጤንነትን ይሰጣሉ።

23 ልብ የሕይወት ምንጭ ስለ ሆነ ልብህን ከሁሉ ነገር አስበልጠህ ጠብቀው።

24 ክፉ ንግግር ከአፍህ አይውጣ፤ ሐሰትንና ማታለልን ከአንተ አርቃቸው።

25 አመለካከትህ ቀጥተኛ ይሁን፤ ግራና ቀኝ ሳትል ወደፊት ተመልከት።

26 እግሮችህ በቀና መንገድ ላይ ይራመዱ። መንገድህም ሁሉ ይቃናልሃል።

27 አቅጣጫህን ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ አታድርግ፤ ወደ ክፉ ነገር ከመሄድ እግርህን መልስ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos