መዝሙር 91 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ጠባቂያችን ነው 1 መጠለያ በመፈለግ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ፥ ሁሉን የሚችለውን አምላክ መጠጊያ የሚያደርግ፥ 2 እግዚአብሔርን “አንተ መከታዬና መጠጊያዬ ነህ፤ አንተ የምተማመንብህ አምላኬ ነህ” ይለዋል። 3 እግዚአብሔር ከተሰወሩ ወጥመዶችና ለሞት ከሚያደርሱ በሽታዎች ይጠብቅሃል። 4 በጥበቃው ሥር ያደርግሃል። እርሱ ስለሚንከባከብህ በሰላም ትኖራለህ፤ የእርሱ ታማኝነት እንደ ጋሻ ወይም እንደ ከተማ ቅጽር ይሆንልሃል። 5 “በሌሊት ሽብር ይደርስብኛል፤ በቀን ፍላጻ ይወረወርብኛል” ብለህ አትፈራም። 6 በጨለማ ከሚመጣ ተላላፊ በሽታና በቀትር ከሚወርድ መቅሠፍት አትሰጋም። 7 አንድ ሺህ በአጠገብህ፥ ዐሥር ሺህ በስተቀኝህ ይወድቃሉ፤ አንተ ግን ከቶ አትጐዳም። 8 ክፉዎች ሲቀጡ በዐይንህ ታያለህ። 9 አንተ እግዚአብሔርን መከታህ፥ ልዑል አምላክንም ጠባቂህ አድርገሃል። 10 ስለዚህ ብርቱ አደጋ አይደርስብህም፤ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይጠጋም። 11 ይህም የሚሆነው በምትሄድበት ሁሉ እንዲጠብቁህ እግዚአብሔር መላእክቱን ስለሚያዛቸው ነው። 12 እግሮችህ ድንጋይ አደናቅፎአቸው እንዳይጐዱ መላእክቱ በእጆቻቸው ይደግፉሃል። 13 አንበሳንና እባብን ትረግጣለህ፤ በአስፈሪው አንበሳና በመርዛሙ እባብ ላይ ትራመዳለህ። 14 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ስለሚወደኝ ከጠላቶቹ እጅ አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም ስለሚያውቅ እጠብቀዋለሁ። 15 በሚጠራኝም ጊዜ እሰማዋለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁም። 16 ዕድሜ እንዲጠግብ አደርገዋለሁ፤ አዳኝነቴንም አሳየዋለሁ።” |