ምሳሌ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምከጥበብ የሚገኝ የጤና በረከት 1 ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ 2 ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል። 3 ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው። 4 በዚያ ጊዜ ሞገስንና ማስተዋልን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ። 5 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ 6 በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል። 7 በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ። 8 ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣ ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል። 9 እግዚአብሔርን በሀብትህ፣ ከምርትህ ሁሉ በኵራት አክብረው፤ 10 ይህን ብታደርግ፣ ጐተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤ መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል። 11 ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ 12 አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና። 13 ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤ 14 እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። 15 ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። 16 በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። 17 መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። 18 ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ። 19 እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤ 20 በዕውቀቱ ቀላያት ተከፈሉ፤ ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ። 21 ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ጥበብና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤ 22 ለነፍስህ ሕይወት፣ ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ። 23 ከዚያም መንገድህን ያለ ሥጋት ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰናከልም፤ 24 ስትተኛ አትፈራም፤ ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል። 25 ድንገተኛን መከራ፣ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤ 26 እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤ እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል። 27 ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። 28 አሁን በእጅህ እያለ፣ ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። 29 አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣ በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት። 30 ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ። 31 በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ። 32 እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል። 33 የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል። 34 እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። 35 ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.