ዘኍል 18:8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፦ “ለእኔ የሚቀርበውን የማይቃጠለውን ልዩ መባ ሁሉ ለአንተ የሰጠሁህ መሆኑን አስታውስ፤ እርሱ ለዘለዓለም ለአንተና ለዘሮችህ ሁሉ ድርሻ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፤ “ለእኔ በሚቀርበው መባ ላይ ኀላፊነትን የሰጠሁህ እኔው ራሴ ነኝ፤ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝም የተቀደሰ መባ ሁሉ ለአንተና ለልጆችህ መደበኛ ድርሻችሁ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው፦ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን እንደ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባኔን ሁሉ ለአንተ እንድትጠብቀው ሰጥቼሃለሁ፤ ለአንተና ለልጆችህ የክህነትህ ድርሻ እንዲሆን ለአንተ የተገባህ አድርጌ ለዘለዓለም ሰጥቼሃለሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው፤ እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የለዩትን የመጀመሪያውን ቍርባኔን ሁሉ ትጠብቁ ዘንድ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ለአንተ እስክታረጅ፥ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ የዘለዓለም ሕግ እንዲሆን ሰጥቼሃለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም አሮንን ተናገረው እንዲህም አለው፦ እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ለእኔ የቀደሱትን የማንሣት ቍርባኔን ሁሉ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ፤ ስለ መቀባትህ ለአንተና ለልጆችህ ድርሻ እንዲሆን ለዘላለም ሰጥቼሃለሁ። |
በተጨማሪም ካህናቱና ሌዋውያኑ ጊዜአቸውን በሙሉ የእግዚአብሔር ሕግ ለሚጠይቀው አገልግሎት ማዋል ይችሉ ዘንድ ለእነርሱ መሰጠት የሚገባውን ሁሉ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች እንዲያመጡ ንጉሡ አዘዘ፤
እስራኤላውያን ይህን የንጉሡን ትእዛዝ እንደ ሰሙ ከእህላቸውና ከወይን ጠጃቸው፥ ከወይራ ዘይታቸውና ከማራቸው ከሌላውም የእርሻቸው ፍሬ ሁሉ ምርጥ የሆነውን በኲራት በልግሥና አበረከቱ፤ ከነበራቸውም ሀብት ሁሉ ዐሥራት አውጥተው ሰጡ፤
አሮንና ልጆቹ ዘወትር ወደ ድንኳን ሲገቡ ወይም በተቀደሰው ስፍራ በክህነት ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ ይለብሱታል፥ በዚህ ዐይነት የውስጥ ሰውነታቸው ስለማይጋለጥ ከሞት ይድናሉ፤ ይህ እንግዲህ ለአሮንና ለትውልዱ ሁሉ ጸንቶ የሚኖር ሥርዓት ነው።
በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት፥ ከቅባቱም ዘይት ጥቂት ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ በአሮን ልጆችና በልብሶቻቸው ላይ ርጨው፤ በዚህ ዐይነት እርሱና ልጆቹ ከነልብሶቻቸው ለእኔ የተለዩ ይሆናሉ።
ሕዝቤ የአንድነት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የእንስሳው ፍርምባና በቀኝ በኩል ያለውን የኋላ እግር ለአሮንና ለልጆቹ ድርሻ ሆኖ እንዲመደብ ወስኛለሁ፤ ውሳኔውም ቋሚ ሥርዓት ይሆናል፤ ይህ እንግዲህ ሕዝቡ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው መባ ነው።
እነርሱም ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን በቀባኸው ዐይነት ቀባቸው፤ በመቀባታቸውም ምክንያት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ካህናት ሆነው ያገለግሉኛል።”
በዚያንም ጊዜ እናንተን ከአሦራውያን የጭቈና አገዛዝ ነጻ አወጣችኋለሁ፤ ከዚያን በኋላ የአገዛዝ ቀንበራቸው ከውፍረታችሁ የተነሣ ይሰበራል እንጂ በእናንተ ጫንቃ ላይ እንደተጫነ አይቀርም።”
“ሊቀ ካህናቱ የቅባት ዘይት በራሱ ላይ የፈሰሰበትና የክህነትንም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ስለ ሆነ፥ ሰው በሞተ ጊዜ ሐዘኑን ለመግለጥ ጠጒሩን አይላጭ፤ ልብሱንም አይቅደድ፤
ካህኑም ከበኲራቱ እንጀራ ከሁለቱ ጠቦቶች ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ እርሱም የካህናቱ ድርሻ ሆኖ ይነሣል፤ እነዚህም ስጦታዎች የተቀደሱ ናቸው።
በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ትውልዱ ከአሮን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ ለእርሱ የተመደበለትን ፈንታ መብላት ይችላል፤ መባውን የሚነካ ሁሉ በቅድስናው ኀይል ይቀሠፋል።”
“ካህኑ በሚሾምበት ቀን መጠኑ በየዕለቱ ከሚቀርበው የእህል መባ ጋር እኩል የሆነ አንድ ኪሎ የላመ ዱቄት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ፤ እርሱም ከፊሉ ጠዋት፥ ከፊሉ ደግሞ ማታ መሥዋዕት ሆኖ ይቅረብ፤
ከእያንዳንዱ የኅብስት ዐይነት አንዱን ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ ያም መባ የእንስሳውን ደም ወስዶ በመሠዊያው ጐን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለረጨው ካህን ድርሻ ይሁን፤
ሙሴ ከቅባት ዘይት ጥቂት እና በመሠዊያው ላይ ከነበረውም ከደሙ ጥቂት ወስዶ በአሮንና በልጆቹ እንዲሁም በልብሳቸው ሁሉ ላይ ረጨው፤ በዚህም ሁኔታ ሙሴ እነርሱንና ልብሶቻቸውን ለእግዚአብሔር የተለዩ አደረገ።
ለእኔ ከሚቀርበው እጅግ ከተቀደሰ መባ ሁሉ፥ ከእህል ቊርባን፥ ስለ ኃጢአት ስርየትና ስለ በደል ካሣ ከሚቀርበውም መባ ሁሉ፥ በእሳት የማይቃጠለው የመባ ድርሻ የአንተና የልጆችህ ነው።
በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙና በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት የሚያቀርቡና የሚያገለግሉ ከመሥዋዕት ተካፍለው እንደሚበሉ ታውቁ የለምን?
ከዚያም እኔ ያዘዝኳችሁን ነገር ሁሉ የምታመጡት እግዚአብሔር አምላካችሁ ለስሙ መጠሪያ ወደ መረጠው ቦታ ይሆናል፤ ይኸውም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትን የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን ሁሉ ታመጡለታላችሁ።
እዚያም የሚቃጠል መሥዋዕታችሁንና ሌላውንም መሥዋዕታችሁን ሁሉ፥ ዐሥራታችሁንና መባችሁን፥ ለእግዚአብሔር የተሳላችሁትንና የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን፥ የከብቶቻችሁንና የበጎቻችሁን በኲር ታቀርባላችሁ፤
“ሌዋውያን ካህናት፥ እንዲያውም፥ መላው የሌዊ ነገድ ከቀሩት የእስራኤል ነገዶች ጋር የርስት ድርሻ የላቸውም፤ በዚህ ምትክ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባ እየተመገቡ ይኖራሉ።
ከዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ በል፦ ‘ከቤቴ የተቀደሰውን ድርሻ ወስጄ ባዘዝከን ትእዛዞች ሁሉ መሠረት ለሌዋውያን፥ ለመጻተኞች፥ ለሙት ልጆችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ሰጥቼአለሁ፤ ከትእዛዞችህም አልተላለፍኩም፤ የዘነጋሁትም ነገር የለም።
ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክህ መረጠህ፤ ከጓደኞችህም ይበልጥ ደስታን በሚሰጥ ቅባት ቀባህ” ይላል።
ከክርስቶስ የተቀበላችሁት መንፈስ በውስጣችሁ ስለሚኖር ሌላ አስተማሪ አያስፈልጋችሁም፤ እርሱ ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ የሚያስተምራችሁም እውነትን ነው እንጂ ሐሰትን አይደለም። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዳስተማራችሁ በክርስቶስ ኑሩ።