ዘሌዋውያን 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ማንም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ንብረት ባለመመለስ እግዚአብሔርን ቢበድል፥ ወይም የሰውን ንብረት በመቀማት፥ ወይም አታሎ በመውሰድ፥ 3 ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም በማለት በሐሰት ቢምል፥ ሰዎች ከሚፈጽሙአቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥ 4 ማንም ሰው እነዚህን በደሎች ፈጽሞ ኃጢአተኛ ቢሆን፥ በቅሚያና በማታለል የወሰደውን፥ በዐደራ የተቀበለውንና ጠፍቶ ያገኘውን ንብረት ይመልስ፤ 5 ወይም በሐሰት ምሎ የወሰደውን ሁሉ አንድ አምስተኛ ጨምሮ ለባለቤቱ ይክፈል። 6 ለበደሉም ማስተስረያ ምንም ነውር የሌለበት አንድ ተባዕት በግ ወይም በታወቀው ተመን የተተመነውን ገንዘብ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ እርሱንም አምጥቶ ለካህኑ ይስጥ። 7 ካህኑም ስለዚያ ሰው ኃጢአት ማስተስረያ በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ በደለኛ ከሆነበት ጉዳይ ሁሉ ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል።” በሙሉ ስለሚቃጠል መሥዋዕት 8 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 9 “ለአሮንና ለልጆቹ የምትሰጣቸው የሥርዓት መመሪያ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ በመሠዊያው ላይ እንዲቈይ ተደርጎ እሳቱ ሲነድ ይደር፤ 10 ካህኑም ከከፈይ የተሠራ ቀሚሱንና ሱሪውን ለብሶ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳት ከበላው በኋላ የቀረውን ዐመድ ሰብስቦ በመሠዊያው ጐን ያፍስሰው። 11 ከዚያም በኋላ ልብሱን ለውጦ ያን ዐመድ ተሸክሞ ከሰፈር ውጪ ያውጣ፤ ንጹሕ በሆነውም ቦታ ይድፋው። 12 በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ሳይጠፋ ሌሊትና ቀን ዘወትር ሲነድ ይኑር፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ የማገዶ እንጨት ይጨምርበት፤ በእርሱ ላይ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አመቻችቶ በማኖር የአንድነት መሥዋዕቱን ስብ ያቃጥለው። 13 እሳቱም ሳይጠፋ በመሠዊያው ላይ ሁልጊዜ ይንደድ። የእህል መባ 14 “ስለ እህል መባ አቀራረብ የተደነገጉት መመሪያዎች እነዚህ ናቸው፦ ትውልዱ ከአሮን ዘር የሆነ ካህን የእህሉን መባ በመሠዊያው ፊት ለፊት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ 15 ከዚህም በኋላ ካህኑ ዘይት ካለበት ከላመ ዱቄት በእፍኙ ወስዶና በእህሉ መባ ላይ ያለውን ዕጣን በሙሉ አንሥቶ ለእግዚአብሔር ያቀረበ መሆኑን ለማሳወቅ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ የዚህም መሥዋዕት መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል። 16 ከእርሱ የተረፈውን ካህናቱ ይበሉታል፤ እርሾ ሳይጨመርበት ተጋግሮ በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ይበሉታል። 17 እርሾ ተጨምሮበት አይጋገርም፤ ከሚነድ ቊርባኔ ለእነርሱ ድርሻ እንዲሆን የሰጠኋቸውና እንደ ኃጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት እጅግ የተቀደሰ ነው። 18 በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ትውልዱ ከአሮን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር ከቀረበው መባ ለእርሱ የተመደበለትን ፈንታ መብላት ይችላል፤ መባውን የሚነካ ሁሉ በቅድስናው ኀይል ይቀሠፋል።” 19 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 20 “ካህኑ በሚሾምበት ቀን መጠኑ በየዕለቱ ከሚቀርበው የእህል መባ ጋር እኩል የሆነ አንድ ኪሎ የላመ ዱቄት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያምጣ፤ እርሱም ከፊሉ ጠዋት፥ ከፊሉ ደግሞ ማታ መሥዋዕት ሆኖ ይቅረብ፤ 21 በዘይት ተለውሶና በሚገባ ተቀላቅሎ እንደ እህል መሥዋዕት ከተጋገረ በኋላ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የእህል መባ ሆኖ ይቅረብ፤ 22 ከአሮን ተወላጆች መካከል ተቀብቶ የክህነትን ሥልጣን የሚረከብ ያን ያዘጋጃል፤ ያም የእግዚአብሔር ቋሚ ድርሻ ስለ ሆነ በሙሉ መቃጠል አለበት። 23 ካህኑ ከሚያቀርበው የእህል መባ ምንም ሳይበላ ሁሉም መቃጠል አለበት።” ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት 24 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 25 “ለአሮንና ለልጆቹ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበው እንስሳ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ። ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው። 26 እንስሳውን የሚሠዋውም ካህን በመገናኛው ድንኳን አደባባይ ባለው የተቀደሰ ስፍራ ይብላው፤ 27 ሰውም ሆነ ማናቸውም ነገር ያን ሥጋ ቢነካ በቅድስናው ኀይል ይቀሠፋል፤ ማናቸውም የልብስ ዐይነት የእንስሳው ደም ቢፈስበት፥ በተቀደሰ ስፍራ ይታጠብ፤ 28 ሥጋ የተቀቀለበት ማናቸውም የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ሥጋው የተቀቀለው በነሐስ ዕቃ ከሆነም ተፈግፍጎ በውሃ ይለቃለቅ። 29 ከካህናቱ ቤተሰብ ወንድ የሆነ ሁሉ ይህን መሥዋዕት ይመገብ፤ እርሱ እጅግ የተቀደሰ መሥዋዕት ነው። 30 ኃጢአትን ለማስወገድ በሚደረገው ሥርዓት ደሙ ወደ ድንኳኑ ውስጥ የገባ ከሆነ ግን እንስሳው መበላት የለበትም፤ ሁሉም በእሳት ይቃጠል።’ |