Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የአሮንና የልጆቹ የክህነት ሹመት
( ዘፀ. 29፥1-37 )

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲሁም የክህነት ልብሱን፥ የቅባቱን ዘይት፥ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበውን ኰርማ ሁለቱን የበግ አውራዎች፥ እርሾ ያልነካው ቂጣ ያለበትን መሶብ፥ አብረህ አምጣ፤

3 ከዚያም የእስራኤልን ሕዝብ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።”

4 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ሕዝቡም ተሰበሰበ፤

5 ሙሴም “እግዚአብሔር እንዲደረግ ያዘዘው ነገር ይህ ነው” አላቸው።

6 ሙሴም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን አቅርቦ በውሃ አጠባቸው፤

7 አሮንን ቀሚስ አልብሶ፥ ካባ ደርቦ፥ መታጠቂያ አስታጠቀው፤ በዚያም ላይ ኤፉድ አደረገለት፤ እርሱንም በልዩ ጥበብ በተጠለፈ ቀበቶ አያይዞ በወገቡ ዙሪያ አሰረለት፤

8 በኤፉዱም ላይ የደረት ኪስ ሰፍቶ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚገለጥባቸውን ኡሪምና ቱሚምን አኖረ፤

9 በራሱም ላይ ጥምጥም አደረገለት፤ በጥምጥሙም ላይ ከፊት ለፊት በኩል እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በወርቅ አጊጦ የተሠራውን የቅድስና ምልክት የሆነውን አክሊል አኖረ።

10 ከዚህም ቀጥሎ ሙሴ የቅባቱን ዘይት ወስዶ የተቀደሰውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትንም ነገሮች ቀባ፤ በዚህ ዐይነት ሁሉንም ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ እንዲሆን አደረገው፤

11 ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ በዚሁ ዐይነት ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለዩ ይሆኑ ዘንድ በመሠዊያውና ለእርሱ መገልገያ በተሠሩት ዕቃዎች ሁሉ ላይ እንዲሁም በመታጠቢያው ሳሕንና በሳሕኑ ማስቀመጫ ላይ ረጨ።

12 የቅባቱንም ዘይት በአሮን ራስ ላይ በማፍሰስ ቀብቶ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ በማድረግ የክህነት ሹመት ሰጠው፤

13 ቀጥሎም ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የአሮንን ወንዶች ልጆች ወደፊት አቅርቦ ቀሚስ አለበሳቸው፤ በወገባቸውም ዙሪያ መታጠቂያ አድርጎ በራሳቸውም ላይ ቆብ ደፋላቸው።

14 ከዚህም በኋላ ሙሴ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርበውን ኰርማ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ በኰርማው ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ፤

15 ሙሴም ዐረደው፤ ከደሙም ጥቂት በጣቱ ነክሮ የመሠዊያውን አራት ማእዘን ጒጦች በመቀባት አንጽቶ ቀደሰው፤ ከዚያም የተረፈውን ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰው፤ በዚህም ዐይነት መሠዊያውን ለእግዚአብሔር በመለየት አነጻው፤

16 ሙሴ በእንስሳው ሆድ ዕቃ ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ ጒበቱን እንደ መረብ ሆኖ የሚሸፍነው ስብ፥ ኲላሊቶቹንና በእነርሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ፥ ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

17 ከኰርማው የቀረውንም ቆዳውን፥ ሥጋውንና አንጀቱን ወስዶ፥ እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት ከሰፈር ውጪ አውጥቶ አቃጠለው።

18 ከዚያም በኋላ ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርበውን የበግ አውራ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ፤

19 ሙሴም ዐረደው፤ ደሙንም በመሠዊያው አራት ማእዘን ረጨ፤

20 የበግ አውራውንም ሥጋ በየብልቱ ቈራረጠ፤ ጭንቅላቱን፥ ብልቶቹንና ስቡን አቃጠለ።

21 እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ የሆድ ዕቃዎቹንና እግሮቹን አጥቦ የአውራ በጉን ሥጋ ሁሉ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቃጠለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መዓዛ ነበር።

22 ሙሴም እንደገና ስለ ክህነት ሹመት የሚቀርበውን ሁለተኛውን አውራ በግ አመጣ፤ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውን በራሱ ላይ ጫኑ፤

23 ሙሴ ዐረደው፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁን አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ቀባ፤

24 ቀጥሎም የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፎች፥ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶችና የቀኝ እግሮቻቸውን አውራ ጣቶች ቀባ፤ ከዚህ የተረፈውንም ደም ሙሴ በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ረጨው።

25 ስቡን፥ ላቱን፥ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ፥ እንደ መረብ ሆኖ ጒበቱን ከሚሸፍነው ስብ ምርጥ የሆነውን ክፍል፥ ኲላሊቶቹን፥ በእነርሱ ላይ ያለውን ስብና በቀኝ በኩል ያለውን ወርች ወሰደ፤

26 በእግዚአብሔር ፊት ካለው እርሾ ያልነካው ቂጣ ከሚቀመጥበትም መሶብ አንድ ኅብስት ወሰደ፤ እንዲሁም በዘይት የታሸ አንድ ኅብስትና አንድ ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ እግሩ ላይ አኖረው፤

27 ይህን ሁሉ ምግብ ወስዶ ለአሮንና ለልጆቹ በእጃቸው አስያዛቸው፤ አነርሱም በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርገው አቀረቡት።

28 ከዚህ በኋላ ሙሴ ምግቡን ከእነርሱ ወሰደ፤ ስለ ክህነት ሹመት መባ እንዲሆን በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ላይ አድርጎ አቃጠለው፤ ይህም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ነበር።

29 ቀጥሎም ሙሴ ፍርምባውን ወስዶ በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ አቀረበ፤ ስለ ክህነት ሹመት ከሚቀርበው የበግ አውራ የሙሴ ድርሻ ይህ ነበር።

30 ሙሴ ከቅባት ዘይት ጥቂት እና በመሠዊያው ላይ ከነበረውም ከደሙ ጥቂት ወስዶ በአሮንና በልጆቹ እንዲሁም በልብሳቸው ሁሉ ላይ ረጨው፤ በዚህም ሁኔታ ሙሴ እነርሱንና ልብሶቻቸውን ለእግዚአብሔር የተለዩ አደረገ።

31 “ሙሴም አሮንንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ አሮንና ልጆቹ ይብሉት ብዬ እንዳዘዝኩት ያን በመሶብ ውስጥ ካለው የተቀደሰ ኅብስት ጋር ብሉት።

32 የተረፈ ሥጋም ሆነ ዳቦ ቢኖር በእሳት አቃጥሉት፤

33 የክህነት ሹመታችሁን ሥርዓት ለመፈጸም ሰባት ቀን ስለሚወስድ ይኸው ሥርዓት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም።

34 ኃጢአታችሁን ለማስወገድ ይህን ዛሬ ያደረግነውን ሥርዓት እንድንፈጽም እግዚአብሔር አዞናል፤

35 ስለዚህም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ በመፈጸም ሰባት ቀን ሙሉ ሌሊትና ቀን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ትቈያላችሁ፤ ይህን ባታደርጉ ግን ትሞታላችሁ፤ ይህ እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሕግ ነው።”

36 አሮንና ልጆቹም በሙሴ አማካይነት እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos