1 ቆሮንቶስ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሐዋርያነት መብት 1 እኔ ነጻነት ያለኝ ሰው አይደለሁምን? እኔ ሐዋርያ አይደለሁምን? እኔ ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ የሥራዬ ውጤት አይደላችሁምን? 2 በጌታ የሐዋርያነቴ ማረጋገጫ ማኅተም እናንተ ስለ ሆናችሁ ለሌሎቹ እንኳ ሐዋርያ ባልሆን ለእናንተ ግን በእርግጥ ሐዋርያ ነኝ። 3 “የሐዋርያነት መብት የለህም” ብለው የሚተቹኝ ቢኖሩ የምሰጠው መልስ ይህ ነው፤ 4 እኛ ምግብና መጠጥ የማግኘት መብት የለንምን? 5 እንደ ሌሎች ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ጴጥሮስም ክርስቲያን ሚስት አስከትለን የመዘዋወር መብት የለንምን? 6 ወይስ በሥራ እየጣርን መኖር የሚገባን በርናባስና እኔ ብቻ ነንን? 7 ያለ ደመወዝ በራሱ ገንዘብ በወታደርነት የሚያገለግል ማነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላስ ማነው? መንጋ እየጠበቀ የመንጋውን ወተት የማይጠጣ ማን ነው? 8 ይህን የምናገረው በሰው አስተሳሰብ ብቻ ነውን? ሕግስ እንዲህ ይል የለምን? 9 “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ በሕግ ተጽፎአል፤ ታዲያ እግዚአብሔር ይህን ያለው ስለ በሬዎች በማሰብ ነውን? 10 እግዚአብሔር ይህን ያለው ስለ እኛ በማሰብ አይደለምን? የሚያርስ ገበሬ በተስፋ እንዲያርስ፥ የሚያበራይም በተስፋ እንዲያበራይ፥ በዚህ ዐይነት ሁሉም ድርሻውን እንዲያገኝ ይህ የተጻፈው በእርግጥ ስለ እኛ ነው። 11 እኛ መንፈሳዊውን ነገር የዘራንላችሁ ከሆነ የእናንተን ሥጋዊ በረከት ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነውን? 12 ሌሎች ይህን ነገር ከእናንተ የመካፈል መብት ያላቸው ከሆነ ታዲያ፥ እኛ ከዚህ የሚበልጥ መብት እንዴት አይኖረንም? እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይህን ማድረጋችንም የክርስቶስ የምሥራች ቃል ከመስፋፋት እንዳይገታ በማሰብ ሁሉን ነገር ታግሠን እንቻል ብለን ነው። 13 በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ምግባቸውን ከቤተ መቅደስ እንደሚያገኙና በመሠዊያው ላይ መሥዋዕት የሚያቀርቡና የሚያገለግሉ ከመሥዋዕት ተካፍለው እንደሚበሉ ታውቁ የለምን? 14 እንዲሁም ደግሞ ወንጌልን የሚያስተምሩ ቀለባቸውን ከዚሁ ሥራቸው እንዲያገኙ ጌታ ደንግጎአል። 15 እኔ ግን በእነዚህ መብቶች በአንዱም አልተጠቀምኩም፤ ይህንንም የጻፍኩት ይህ መብቴ ሳይከበርልኝ ለምን ቀረ? በማለት አይደለም። ሰው ትምክሕቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ይልቅ ብሞት ይሻለኛል። 16 ወንጌልን ማስተማር ግዴታዬ ስለ ሆነ የምመካበት ነገር አይደለም፤ እንዲያውም ወንጌልን ሳላስተምር ብቀር ወዮልኝ! 17 የወንጌልን ቃል ያለ ግዴታ በፈቃዴ ባበሥር የድካም ዋጋ ይኖረኛል፤ በግዴታ ባደርገው ግን በዐደራ የተሰጠኝን ኀላፊነት ፈጸምኩ እንጂ ሌላ ያደረግኹት ነገር አለ ማለት አይደለም። 18 ታዲያ፥ የድካሜ ዋጋ ምንድን ነው? እንግዲህ የድካሜ ዋጋ ወንጌልን በማስተማሬ ያለኝን መብት ሳልጠቀምበት ወንጌልን የማስተማር ሥራዬን ያለ ደመወዝ በነጻ መፈጸም ነው። 19 እኔ የማንም ባሪያ ሳልሆን ነጻ ሰው ነኝ፤ ይሁን እንጂ በተቻለኝ መጠን ብዙዎቹን በማዳን ለመጥቀም ብዬ የሁሉም ባሪያ ሆኜአለሁ። 20 ከአይሁድ ጋር ስሆን አይሁድን ለማዳን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ፤ እኔ ከሕግ በታች ባልሆንም እንኳ ከሕግ በታች ያሉትን ለማዳን ስል ከሕግ በታች እንዳሉት ሰዎች ሆንኩ። 21 እኔ የእግዚአብሔር ሕግ ያለኝና ከክርስቶስ ሕግ ሥር ብሆንም እንኳ ሕግ የሌላቸውን አሕዛብ ለማዳን ስል ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንኩ። 22 በእምነት ደካሞች የሆኑትን ለማዳን ስል እንደ ደካሞች ደካማ ሆንኩ፤ በተቻለ መጠን ጥቂቶችን ለማዳን ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንኩ። 23 ይህን ሁሉ ማድረጌ የወንጌልን በረከት ለመካፈል ስለ ወንጌል ብዬ ነው። 24 በሩጫ ውድድር ሁሉም እንደሚሮጡና ከእነርሱም አንዱ ብቻ ሽልማት እንደሚቀበል ታውቁ የለምን? ስለዚህ እናንተም ሽልማትን ለመቀበል ሩጡ። 25 በሩጫ የሚወዳደሩ ሁሉ አድካሚ ልምምድ ያደርጋሉ፤ እነርሱ እንዲህ የሚደክሙት የሚጠፋውንና ጊዜያዊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ነው፤ እኛ ግን የምንደክመው የማይጠፋውንና ዘለዓለማዊ የሆነውን አክሊል ለማግኘት ነው። 26 እኔ ግን ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም፤ ነፋስን በቡጢ እንደሚመታ ሰው በከንቱ የምሰነዝር ሰው አይደለሁም። 27 ስለዚህ ሌሎችን ወደ ውድድር ከጠራሁ በኋላ እኔ ራሴ ከውድድሩ ውጪ ሆኜ እንዳልገኝ ሰውነቴን እየተቈጣጠርኩ እንዲታዘዝልኝ አደርገዋለሁ። |