ዘሌዋውያን 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየበዓላት አከባበር 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የተቀደሱ ብላችሁ የምታውጁአቸው የእኔ የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው፤ 3 ሥራ የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች አሉላችሁ፤ ሰባተኛው ዕለተ ሰንበት ግን የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚያን ቀን ለአምልኮ ተሰብሰቡ እንጂ ምንም ሥራ አትሥሩበት፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ሰንበት ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕለት ነው፤ 4 ለእያንዳንዳቸው በተወሰነላቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት እየተሰበሰባችሁ የምታከብሩአቸው ዋና ዋናዎቹ በዓላት እነዚህ ናቸው። የፋሲካና የቂጣ በዓል ( ዘኍ. 28፥16-25 ) 5 “እግዚአብሔር የሚከበርበት የፋሲካ በዓል የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጀንበር ጠልቃ መሸትሸት ሲል ይጀመራል፤ 6 በዐሥራ አምስተኛው ቀን የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ከዚያን በኋላ እስከ ሰባት ቀን ድረስ እርሾ ያልነካው ቂጣ ትመገባላችሁ። 7 ከእነዚህ ዕለቶች በመጀመሪያው ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ ከዕለት ተግባራችሁ ማንኛውንም በዚህ ቀን አትሠሩም። 8 እስከ ሰባት ቀን ድረስ የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የዕለት ተግባራችሁን ማከናወን ትታችሁ በሰባተኛው ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ።” 9 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 10 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ እግዚአብሔር ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምታጭዱበት ጊዜ የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ ስጡ፤ 11 እግዚአብሔር ይቀበላችሁ ዘንድ ካህኑ ነዶውን በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል። ካህኑም እርሱን ማቅረብ ያለበት ከሰንበት ቀጥሎ በሚውለው ቀን ነው። 12 የእህል መባችሁን በምታቀርቡበት በዚያኑ ቀን ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሆነውን የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ አብራችሁ አቅርቡ። 13 ከእርሱም ጋር በወይራ ዘይት የተለወሰ ሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት የምግብ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ይህም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል፤ ከዚህም ጋር አንድ ሊትር የሚሆን የወይን ጠጅ ስጦታ ታቀርባላችሁ። 14 ይህንንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ከማቅረባችሁ በፊት ከአዲሱ እህል ጥሬውን ወይም የተቈላውን ወይም እንጀራ ጋግራችሁ አትብሉ። ይህም ድንጋጌ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኑር። የመከር በዓል ( ዘኍ. 28፥26-31 ) 15 “ነዶአችሁን ለእግዚአብሔር በመወዝወዝ የሚቀርብ ልዩ መባ አድርጋችሁ ካመጣችሁበት ሰንበት ማግስት ጀምሮ ሰባት ሳምንት ቊጠሩ፤ 16 ከሰባተኛው ሰንበት በኋላ በኀምሳኛው ቀን እንደገና የአዲስ እህል ቊርባን ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ 17 እያንዳንዱ ቤተሰብ ሁለት እንጀራ በመወዝወዝ ልዩ መባ አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ እያንዳንዱ እንጀራ እርሾ ገብቶበት ከሁለት ኪሎ የላመ ዱቄት ጋር ተጋግሮ ስለሚሰበሰበው አዲስ መከር ለእግዚአብሔር የበኲራት መባ ሆኖ ይቅረብ። 18 ከእንጀራውም ጋር ማኅበሩ ምንም ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰባት የበግ ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ያምጡ፤ እነርሱም ከእህሉ ቊርባንና ከወይን ጠጁ መባ ጋር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት ሆነው ይቀርባሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርበው መሥዋዕት ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 19 ከዚያም ቀጥሎ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አንድ ተባዕት ፍየል፤ ለአንድነት መሥዋዕት የአንድ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ 20 ካህኑም ከበኲራቱ እንጀራ ከሁለቱ ጠቦቶች ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ እርሱም የካህናቱ ድርሻ ሆኖ ይነሣል፤ እነዚህም ስጦታዎች የተቀደሱ ናቸው። 21 በዚያም ቀን የአምልኮ ስብሰባ እንዲሆንላችሁ ታውጃላችሁ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ ይህ በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው። 22 “የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር አትጨዱ፤ የመከሩንም ቃርሚያ ለመሰብሰብ ወደ ኋላ አትመለሱ፤ እርሱን ለድኾችና ለመጻተኞች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” የመለከት በዓል ( ዘኍ. 29፥1-6 ) 23 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ በሰባተኛው ወር፥ ወሩ በገባ በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔርን ለማምለክ በመለከት የታወጀ መታሰቢያ የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ። 25 በዚያን ዕለት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡበት እንጂ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት።” የኃጢአት ስርየት ቀን ( ዘኍ. 29፥7-11 ) 26 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 27 “በዚህ በሰባተኛው ወር ዐሥረኛው ቀን የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረያ ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው፤ በዚያን ዕለት እግዚአብሔርን ለማምለክ ትሰበሰባላችሁ፤ ለንስሓም ሰውነታችሁን አዋርዱ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡ፤ 28 በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት የሕዝቡን ኃጢአት የማስወገድ ሥርዓት የሚፈጸምበት ዕለት ስለ ሆነ፥ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አትሥሩበት። 29 በዚያን ዕለት በንስሓ ራሱን የማያዋርድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ 30 በዚያን ዕለት ሥራ የሚሠራ ማንም ሰው ቢኖር ከሕዝብ ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ 31 ስለዚህ በዚያን ዕለት ምንም ሥራ እንዳትሠሩ፤ ይህም የሥርዓት መመሪያ በምትኖሩበት ቦታ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ተጠብቆ ይኖራል። 32 ወሩ ከገባ ከዘጠነኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዐሥረኛው ቀን የፀሐይ መጥለቂያ ጊዜ ድረስ ለንስሓ ራሳችሁን አዋርዱ፤ ይህን ዕለት ልዩ የዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ጠብቁት።” የዳስ በዓል ( ዘኍ. 29፥12-40 ) 33 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 34 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በዚህ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይከበራል። 35 ከእነዚህም ቀኖች በመጀመሪያው ዕለት እግዚአብሔርን የምታመልኩበት በዓል ይሁን እንጂ ምንም ሥራ አትሥሩበት፤ 36 ከሰባቱም ቀኖች በእያንዳንዱ ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ታደርጋላችሁ፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል የምግብ መሥዋዕት አቅርቡ፤ ይህም ጉባኤውን የምትፈጽሙበት ቀን ስለ ሆነ ምንም ሥራ አትሥሩበት። 37 “የምግብ መባ፥ የሚቃጠል መሥዋዕት፥ የእህሉን ቊርባን፥ መሥዋዕቱንና የመጠጡንም ቊርባን፥ በየተወሰነው ቀን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ስብሰባዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው። 38 እነዚህም በዓላት ከእግዚአብሔር ሰንበቶች ጋር ተጨማሪ ሆነው የሚከበሩ ናቸው፤ ለእግዚአብሔር ከምትሰጡት ስጦታ ስእለት ሲፈጸምላችሁ ከምትሰጡት ስጦታና በፈቃዳችሁ ከምታቀርቡት ሁሉ ጋር ተደምረው የሚቀርቡ ናቸው። 39 “የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ሰባተኛው ወር ከገባ ከዐሥራ አምስተኛው ቀን በመጀመር ይህን የደስታ በዓል በእግዚአብሔር ፊት እስከ ሰባት ቀን ድረስ ታከብራላችሁ፤ መጀመሪያውና ስምንተኛው ቀን ልዩ የዕረፍት ቀን ይሆናል። 40 በዚያም በመጀመሪያው ቀን ከምድራችሁ ዛፎች ምርጥ ፍሬ፥ የዘንባባ ዝንጣፊና የለምለም ዛፍ ቅርንጫፍ የወንዝ አኻያ ዛፍ ይዛችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት እየተደሰታችሁ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በዓል አድርጉ። 41 ይህንንም በዓል በየዓመቱ በሰባተኛው ወር ለሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በደስታ አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጆቻችሁ የዘለዓለም ሥርዓት ነው፤ 42 ለሰባት ቀኖች በዳሶች ትቀመጣላችሁ፤ መላው የእስራኤል ሕዝብ በዳስ ይቀመጣሉ። 43 ስለዚህም እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ምድር ባወጣሁ ጊዜ ዳሶችን እየጣሉ እንዲኖሩ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” 44 በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔርን ለማክበር ስለሚጠብቁአቸው የሃይማኖት በዓላት ይህን መመሪያ ለእስራኤል ሕዝብ ሰጠ። |