ሉቃስ 12:19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህም በኋላ ራሴን፦ እነሆ፥ ለብዙ ዓመት የሚበቃህ ብዙ ሀብት አለህ፤ እንግዲህ ዕረፍት በማድረግ ተዝናና! ብላ! ጠጣ! ደስ ይበልህ! እለዋለሁ’ አለ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ነፍሴንም አንቺ ነፍሴ! ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስ ይበልሽ እላታለሁ፤’ አለ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሰውነቴንም እንዲህ እላታለሁ፦ ሰውነቴ ሆይ፥ የሰበሰብሁልሽ ለብዙ ዓመታት የሚበቃሽ የደለበ ብዙ ሀብት አለሽ፤ እንግዲህ ወዲህ ዕረፊ፥ ብዪ፤ ጠጪም፤ ደስም ይበልሽ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ነፍሴንም፦ አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። |
ወጣት ሆይ! ወጣትነት እጅግ ግሩም ስለ ሆነ በወጣትነትህ ዘመን ደስ ይበልህ፤ በልብህም ሐሤት አድርግ፤ ዐይንህ የሚያየውንና ልብህ የሚመኘውን ሁሉ ፈጽም፤ ሆኖም ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ ዕወቅ።
እንግዲህ ለሰው የሚጠቅመው ነገር ቢኖር፥ ደክሞ በመሥራት ያፈራውን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት ራሱን ለማስደሰት መቻሉ ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጠ መሆኑን ተረድቼአለሁ።
እናንተ ግን ጥሪውን በመቀበል ፈንታ በዓል አደረጋችሁ፤ የምትበሉትንም በግና በሬ ዐረዳችሁ፤ ወይን ጠጅም ጠጥታችሁ “ነገ እንሞታለን ዛሬ እንብላ እንጠጣ!” አላችሁ።
በአገሪቱ ላይ መኖር የሚገባችሁ እናንተ ብቻ መስሎአችሁ፥ ቀድሞ በነበራችሁ ይዞታ ላይ ለመቀላቀል ሰዎችን ሁሉ እያስወጣችሁ ቤትን ከቤት ማያያዝና እርሻንም በእርሻ ላይ ለመቀላቀል ለምትፈልጉ ወዮላችሁ!
እንዲህም አለ፦ ‘የማደርገው ይህ ነው፤ ጐተራዎቼን ሁሉ አፈርስና ሌሎች ትልልቅ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያ እህሌንና ንብረቴን ሁሉ ሰብስቤ አከማቻለሁ።
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ! አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይይዛችኋል።
እንደ ሰው አስተሳሰብ እኔ በኤፌሶን ከአራዊት ጋር መታገሌ ጥቅሜ ምንድን ነው? ሙታን ከሞት የማይነሡ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት ኑ እንብላ፤ እንጠጣ” እንደ ተባለው መሆኑ ነው።
የእነርሱ አምላክ ሆዳቸው ነው፤ አሳፋሪ የሆነ ነገር ለእነርሱ ክብራቸው ነው፤ ሐሳባቸውም የሚያተኲረው በምድራዊ ነገር ላይ ነው፤ ስለዚህ የእነርሱ መጨረሻ ጥፋት ነው።
የዚህ ዓለም ሀብታሞች እንዳይታበዩ ወይም ተስፋቸውን አስተማማኝ ባልሆነ ሀብት ላይ እንዳያደርጉ እዘዛቸው፤ እንዲሁም ተስፋቸው እኛን ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን እዘዛቸው።
አሕዛብ እንደሚያደርጉት በስድነት፥ በፍትወት፥ በስካር፥ ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ፥ ያለ ልክ ጠጥቶ በመጨፈርና አጸያፊ በሆነ የጣዖት አምልኮ ያሳለፋችሁት ዘመን ይበቃል።
እርስዋ ለራስዋ ክብርንና ምቾትን የሰጠችውን ያኽል ሥቃይና ሐዘን ስጡአት፤ እርስዋ በልብዋ ‘እንደ ንግሥት ተቀምጬአለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ከቶ አይደርስብኝም’ በማለት ትመካለች።
ከዚያም በኋላ ዳዊትን ወራሪዎቹ ወዳሉበት እየመራ አደረሰው። ወራሪዎቹም በየቦታው ተበታትነው በመብላትና በመጠጣት ተድላ ደስታ በማድረግ ላይ ነበሩ፤ ከፍልስጥኤምና ከይሁዳ ያገኙት ምርኮ እጅግ ብዙ ነበር፤