1 ሳሙኤል 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበዐማሌቃውያን ላይ የተደረገ ጦርነት 1 ዳዊትና ተከታዮቹ በሦስተኛው ቀን ወደ ጺቅላግ ሲደርሱ ዐማሌቃውያን ኔጌብንና ጺቅላግን ወረው ነበር፤ በጺቅላግም ላይ አደጋ ጥለው አቃጠሉአት። 2 ሴቶችንና በውስጡም የነበሩትን ሁሉ ማርከው ወስደዋል፤ ከዚያም ለቀው ሲሄዱ ያገኙትን ሁሉ ማርከው ወሰዱ እንጂ ማንንም አልገደሉም ነበር፤ 3 ዳዊትና ተከታዮቹም እዚያ በደረሱ ጊዜ ከተማይቱ ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸው፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ተማርከው መወሰዳቸውን ተረዱ፤ 4 ዳዊትና ተከታዮቹም ፈጽሞ እስኪደክሙ ድረስ ባለማቋረጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ። 5 ሁለቱ የዳዊት ሚስቶች የኢዝራኤላይቱን አሒኖዓምና የቀርሜሎሳይቱ የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌል ተማርከው ነበር። 6 ሰዎቹ ሁሉ በሴቶችና ወንዶች ልጆቻቸው መማረክ ምክንያት ተማርረው ስለ ነበረ በድንጋይ ሊወግሩት በመነጋገራቸው ዳዊት በታላቅ አደጋ ላይ ነበር። እርሱ ግን በአምላኩ በእግዚአብሔር ልቡን አጽናና፤ 7 ዳዊትም የአቤሜሌክን ልጅ ካህኑን አብያታርን “ኤፉዱን አምጣልኝ” አለው፤ አብያታርም ኤፉዱን አመጣለት፤ 8 ዳዊትም “እነዚያን ወራሪዎች ተከታትዬ በማሳደድ ልያዛቸውን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “ተከተላቸው! እነርሱንም ይዘህ ምርኮኞችን በመታደግ ታድናለህ” ሲል መለሰለት። 9 ስለዚህም ዳዊትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ተከታዮቹ ወጥተው ሄዱ፤ ብሦር ተብሎ በሚጠራው ወንዝ አጠገብ በደረሱ ጊዜ፥ ጥቂቶቹ በዚያ ዕረፍት በማድረግ ቈዩ። 10 ዳዊት ግን ከአራት መቶ ተከታዮቹ ጋር ማሳደዱን ቀጠለ፤ ሌሎቹ ሁለት መቶ ተከታዮቹ ግን ወንዙን ለመሻገር ስለ ደከሙ ወደ ኋላ ቀሩ። 11 አንድ ግብጻዊ ወጣት ከበረሓ ሲመጣ አግኝተው ወደ ዳዊት አቀረቡት፤ እነርሱም የሚመገበው እህል ሰጥተውት በላ፤ ውሃም አጠጡት። 12 ደረቅ የበለስ ፍሬና ሁለት ጥፍጥፍ ዘቢብ አቀረቡለት፤ ወጣቱም ከተመገበ በኋላ እንደገና በረታ፤ ከዚያ በፊት ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እህል ውሃ አልቀመሰም ነበር። 13 ዳዊትም ወጣቱን “የማን አገልጋይ ነህ? አመጣጥህስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቀው። ወጣቱም “እኔ ግብጻዊ የሆንኩ የአንድ ዐማሌቃዊ አገልጋይ ነኝ፤ ታምሜ ስለ ነበር ከሦስት ቀን በፊት ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ፤ 14 ይህም ከመሆኑ በፊት በይሁዳ ደቡብ የምትገኘውን የከሪታውያንን ግዛትና የካሌብን ግዛት በመውረር ጺቅላግን አቃጥለናታል” ሲል መለሰለት። 15 ዳዊትም “እነዚያ ወራሪዎች ወዳሉበት ስፍራ ልትመራን ትችላለህን?” ሲል ጠየቀው። ወጣቱም “እንደማትገድለኝና ለጌታዬም አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ ከማልክልኝ ላሳይህ እችላለሁ” ሲል መለሰለት። 16 ከዚያም በኋላ ዳዊትን ወራሪዎቹ ወዳሉበት እየመራ አደረሰው። ወራሪዎቹም በየቦታው ተበታትነው በመብላትና በመጠጣት ተድላ ደስታ በማድረግ ላይ ነበሩ፤ ከፍልስጥኤምና ከይሁዳ ያገኙት ምርኮ እጅግ ብዙ ነበር፤ 17 በምሽት ጊዜ ዳዊት በእነርሱ ላይ አደጋ ጥሎ እስከ ማግስቱ ማታ ድረስ ተዋጋቸው፤ በግመል ላይ ተቀምጠው እየጋለቡ ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር ከነዚያ ወራሪዎች ያመለጠ አንድም አልነበረም፤ 18 ዳዊትም ዐማሌቃውያን የወሰዱበትን ማንኛውንም ሰውና ንብረት፥ እንዲሁም ሁለቱን ሚስቶቹን ጭምር አዳነ፤ 19 አንድም የጐደለ ሳይኖር ዳዊት የተከታዮቹን ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ እንዲሁም ዐማሌቃውያን ማርከው የወሰዱትን ምርኮ ሁሉ አስመለሰ፤ 20 የከብት፥ የበግና የፍየል መንጋዎችንም ሁሉ አገኘ፤ ተከታዮቹም እንስሶቹን በፊታቸው እየነዱ “ይህ ሁሉ የዳዊት ምርኮ ነው!” አሉ። 21 ዳዊትም ደክሞአቸው በብሦር ምንጭ አጠገብ ዕረፍት በማድረግ ቈይተው ወደነበሩት ወደ ሁለት መቶ ተከታዮቹ ተመልሶ ሄደ። እነርሱም ዳዊትንና ተከታዮቹን ሊቀበሉአቸው መጡ፤ ዳዊትም ወደ እነርሱ ቀረብ ብሎ ደኅንነታቸውን በመጠየቅ ሰላምታ አቀረበላቸው። 22 ነገር ግን ከዳዊት ጋር አብረው ከሄዱት መካከል የብልግና ጠባይ ያለባቸው አንዳንድ የማይረቡ ሰዎች “ከእኛ ጋር ወደ ጦርነቱ ስላልሄዱ ምርኮ ልናካፍላቸው አይገባም፤ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ብቻ ተረክበው ወዲያ ይሂዱ” አሉ። 23 ዳዊትም “ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔር በሰጠን ድል እናንተ ይህን ማድረግ አትችሉም! እኛን በሕይወት ጠብቆ በወራሪዎች ላይ ድልን የሰጠን እርሱ ነው፤ 24 እናንተ በምትሉት ነገር ማንም አይስማማበትም! ወደ ኋላ ቀርቶ ጓዝ ሲጠብቅ የቈየውም ሆነ ወደ ጦርነት የዘመተው ሁሉም የተገኘውን ምርኮ እኩል መካፈል አለበት” ሲል መለሰላቸው። 25 ዳዊትም ከዚያን ቀን ጀምሮ ይህን እንደ ሕግና ሥርዓት አድርጎ ስለ ተጠቀመበት በእስራኤል ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሲሠራበት ይኖራል። 26 ዳዊትም ወደ ጺቅላግ በተመለሰ ጊዜ ከምርኮው ከፊሉን ወዳጆቹ ለሆኑት ለይሁዳ ሽማግሌዎች ላከላቸው፤ ከላከላቸውም ምርኮ ጋር “ይህ ከእግዚአብሔር ጠላቶች ተወስዶ የተላከላችሁ ስጦታ ነው” የሚል መልእክት ነበር፤ 27 ከዚያም ምርኮ በቤትኤል ለሚገኙ፥ በይሁዳ ደቡብ በራማ ለሚገኙ፥ እንዲሁም በያቲር ከተሞች ለሚገኙ ወገኖች ሁሉ ላከላቸው፤ 28 ከዚህም በቀር በዓሮዔር፥ በሲፍሞት፥ በኤሽተሞዓና፥ 29 በራካል ለሚገኙ፥ እንዲሁም ለይራሕመኤል ጐሣ ለቄናውያን፥ 30 በሖርማ፥ በቦርዓሻን፥ በዐታክና፥ 31 በኬብሮን ከተሞች ለሚኖሩ ሁሉ ላከላቸው፤ ከዚህም በቀር እርሱና ተከታዮቹ በተዘዋወሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ ለሚኖሩ ሰዎች ስጦታ ላከ። |