ምሳሌ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ጥበበኛ ሴት ቤትዋን በሥነ ሥርዓት ታስተዳድራለች፤ ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጅዋ ታፈርሰዋለች። 2 አካሄዱ ቀጥተኛ የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ሰው ግን እግዚአብሔርን አይፈራም። 3 ሞኝን የገዛ ንግግሩ ያስቀጣዋል፤ ጥበበኞችን ግን መልካም አነጋገራቸው ይጠብቃቸዋል። 4 የምታርስባቸው በሬዎች ከሌሉህ ጐተራህ ባዶ ይሆናል። በሬዎች ካሉህ ግን ጐተራህ በእህል የተሞላ ይሆናል። 5 ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን የሚናገረው ሐሰት ነው። 6 ፌዘኛ ሰው ጥበብን ይፈልጋል፤ አያገኛትም። አስተዋዮች ግን ዕውቀትን በቀላሉ ይገበያሉ። 7 ከእነርሱ የምትማረው ምንም ዕውቀት ስለሌለ ከሞኞች ራቅ። 8 የብልኅ ሰው ጥበብ መንገዱን እንዳይስት ያደርገዋል። ሞኝን ሰው ግን ሞኝነቱ መንገዱን እንዲስት ያደርገዋል። 9 ሞኞች ኃጢአት ሲሠሩ በመጸጸት ፈንታ ያፌዛሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይፈልጋሉ። 10 ደስታህም ሆነ ሐዘንህ የራስህ ነው፤ ማንም የሚካፈልህ የለም። 11 የክፉ ሰው ቤት ይፈርሳል፤ የደግ ሰው ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል። 12 አንተ “ትክክለኛ መንገድ ነው” ብለህ የምታስበው ወደ ሞት ይመራህ ይሆናል። 13 በሳቅ ጊዜ እንኳ በልብ ውስጥ ሐዘን ሊኖር ይችላል፤ የደስታም ፍጻሜ ለቅሶ ነው። 14 ከሐዲዎች ሰዎች የክፉ ሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ። 15 ሞኝ ሰው የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል፤ ብልኆች ግን እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይመረምራሉ። 16 ብልኆች እግዚአብሔርን ስለሚፈሩ ከክፉ ነገር ለመራቅ ይጠነቀቃሉ፤ ሞኞች ግን ከአደጋ የማይጠነቀቁ ችኲሎች ናቸው። 17 ቊጡ ሰው የሞኝነትን ሥራ ይሠራል፤ ጥበበኛ ግን ይታገሣል። 18 አላዋቂዎች የስንፍናቸውን ዋጋ ይቀበላሉ፤ ብልኆች ግን ዕውቀትን እንደ አክሊል ይቀዳጃሉ። 19 ክፉዎች በደጋግ ሰዎች ፊት ይንበረከካሉ፤ ኃጢአተኞች በጻድቃን ደጅ ያጐነብሳሉ። 20 ድኻ ሰው በጐረቤቱ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው። ሀብታሞች ግን ብዙ ወዳጆች አሉአቸው። 21 ሰዎችን የሚንቅ ኃጢአተኛ ነው፤ ለድኾች የሚራራ ግን የተባረከ ነው፤ 22 ክፉ የሚያቅዱ ሰዎች ስሕተተኞች አይደሉምን? መልካምን ነገር የሚያቅዱ ግን ምሕረትንና ታማኝነትን ያገኛሉ። 23 ተግቶ መሥራት ጥቅምን ያስገኛል፤ ወሬኛነት ግን ያደኸያል። 24 የብልኆች ዘውድ ጥበባቸው ነው፤ የሞኞች ጌጥ ግን ሞኝነታቸው ነው። 25 እውነትን የሚናገር ምስክር ሕይወትን ያድናል፤ ሐሰት የሚናገር ምስክር ግን አታላይ ነው። 26 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጽኑ መታመኛና ዋስትና አለው። 27 እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስለዚህ ከሞት ወጥመድ ለማምለጥ ከፈለግህ እግዚአብሔርን ፍራ። 28 የንጉሥ ታላቅነት የሚለካው በሚያስተዳድራቸው ሕዝብ ብዛት ነው፤ የሚገዛው ሕዝብ ከሌለው ግን ለንጉሡ ጥፋት ነው። 29 ትዕግሥተኛ ብትሆን አስተዋይ መሆንህን ትገልጣለህ፤ ቊጡ ብትሆን ግን ስንፍናህን ታሳያለህ። 30 ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል፤ ቅንአት ግን አጥንትን ያደቃል። 31 ድኾችን ማስጨነቅ ፈጣሪን መናቅ ነው፤ ለድኾች ቸርነትን ማድረግ ግን እግዚአብሔርን እንደ ማክበር ይቈጠራል። 32 ችግር ሲመጣ ክፉዎች ይወድቃሉ፤ ጻድቃን ግን በታማኝነታቸው ይጠበቃሉ። 33 የአስተዋይ ሰው ልብ ጥበብን የተሞላ ነው፤ በሞኞች ልብ ግን ጥበብ አትታወቅም። 34 እውነተኛነት አንድን ሕዝብ ታላቅ ያደርገዋል፤ ኃጢአት ግን ማንኛውንም ሕዝብ ያዋርዳል። 35 ነገሥታት ችሎታ ባላቸው አገልጋዮች ይደሰታሉ፤ አሳፋሪ አገልጋዮች ግን ንጉሡን ያስቈጣሉ። |