Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሉቃስ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የመበለቲቱ ስጦታ
( ማር. 12፥41-44 )

1 ኢየሱስ ቀና ብሎ ሲመለከት ሀብታሞች መባቸውን በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ውስጥ ሲጨምሩ አየ።

2 እንዲሁም አንዲት ድኻ መበለት፥ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በሣጥኑ ውስጥ ስትጨምር አየ።

3 እንዲህም አለ፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት፥ ከሁሉም አብልጣ ሰጥታለች።

4 እነርሱ የሰጡት ከሀብታቸው የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።”


ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስ የኢየሱስ ትንቢት
( ማቴ. 24፥1-2 ፤ ማር. 13፥1-2 )

5 አንዳንድ ሰዎች፥ “ይህ ቤተ መቅደስ እንዴት ውብ ነው? በከበሩ ድንጋዮችና ለእግዚአብሔር በቀረቡ ስጦታዎች አጊጦአል” እያሉ ይነጋገሩ ነበር።

6 ኢየሱስ ግን “ይህ የምታዩት ሁሉ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ አንድ ቀን ይፈራርሳሉ።”

7 እነርሱም “መምህር ሆይ! ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን የምናውቅበት ምልክት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።


ከጌታ መምጣት በፊት የሚደርስ ስደትና መከራ
( ማቴ. 24፥3-14 ፤ ማር. 13፥3-13 )

8 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እንዳትሳሳቱ ተጠንቀቁ! ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ! እነሆ፥ ጊዜው ቀርቦአል!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እነርሱን አትከተሉአቸው።

9 ስለ ጦርነትና ስለ ሁከት በምትሰሙበት ጊዜም አትደንግጡ፤ አስቀድሞ ይህ ይሆን ዘንድ ይገባል፤ ይሁን እንጂ ፍጻሜው ወዲያውኑ አይሆንም።”

10 ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል።

11 በየቦታውም ብርቱ የምድር መናወጥ፥ ራብና ወረርሽኝ ይሆናል። የሚያስፈሩ ነገሮችና ታላላቅ ምልክቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ።

12 ነገር ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሰዎች እናንተን ይይዙአችኋል፤ ያሳድዱአችኋል፤ ወደ ምኲራብና ወደ ወህኒ ቤትም አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ስለ ስሜም ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎች ይወስዱአችኋል።

13 ይህም ስለ ስሜ ለመመስከር መልካም አጋጣሚ ይሆንላችኋል።

14 ስለዚህ በሚቀርብባችሁ ክስ ስለምትሰጡት መልስ መጨነቅ እንደማይገባችሁ አስቀድማችሁ ልብ አድርጉ።

15 ከጠላቶቻችሁ ማንም ሊቋቋመው ወይም ሊቃወመው የማይችለውን አንደበትና ጥበብ እኔ እሰጣችኋለሁ።

16 ወላጆቻችሁና ወንድሞቻችሁ፥ ዘመዶቻችሁና ወዳጆቻችሁም ሳይቀሩ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ከእናንተ አንዳንዶቹ ይገደላሉ።

17 ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።

18 ነገር ግን ከራሳችሁ ጠጒር አንዲት እንኳ አትጠፋም።

19 በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ” አለ።


ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት አስቀድሞ እንደ ተናገረ
( ማቴ. 24፥15-21 ፤ ማር. 13፥14-19 )

20 ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም በጠላት ወታደሮች ተከባ ባያችሁ ጊዜ ለመጥፋት እንደ ተቃረበች ዕወቁ፤

21 በዚያን ጊዜ በይሁዳ ምድር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በከተማይቱ ውስጥ ያሉ ከዚያ ይውጡ፤ ከከተማ ውጪ ያሉትም ወደ ከተማይቱ አይግቡ።

22 ስለዚህ ጥፋት የተጻፈው ትንቢት እንዲፈጸም ይህ የበቀልና የቅጣት ጊዜ ነው።

23 በዚያን ጊዜ ለነፍሰጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! በምድር ላይ ታላቅ መከራ ይሆናል፤ በዚህም ሕዝብ ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል።

24 ከእነርሱም ብዙዎች በሰይፍ ይገደላሉ፤ ሌሎችም ተማርከው ወደየአገሩ ይወሰዳሉ። የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ኢየሩሳሌም በአሕዛብ የተረገጠች ትሆናለች።”


የሰው ልጅ ዳግመኛ መምጣት
( ማቴ. 24፥29-31 ፤ ማር. 13፥24-27 )

25 ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በፀሐይና በጨረቃ፥ በከዋክብትም ላይ ድንቅ ምልክቶች ይታያሉ፤ በምድርም ላይ ሕዝቦች ሁሉ ከባሕርና ከማዕበሉ አስደንጋጭ ድምፅ የተነሣ ፈርተው ይጨነቃሉ።

26 በዓለም ላይ የሚመጣውን ነገር በመጠባበቅ ሰዎች በፍርሃት ይሸበራሉ፤ በዚያን ጊዜ የሰማይ ኀይሎች ይናወጣሉ፤

27 ከዚህም በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ላይ ሆኖ ሲመጣ ሰዎች ያዩታል።

28 ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ መዳናችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ።”


የጌታን መምጫ የምታመለክት የበለስ ዛፍ ምሳሌ
( ማቴ. 24፥32-35 ፤ ማር. 13፥28-31 )

29 ቀጥሎም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “የበለስን ዛፍና የሌሎችንም ዛፎች ሁኔታ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤

30 ቅጠሎቻቸው ሲያቈጠቊጡ ባያችሁ ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ።

31 በዚህ ዐይነት ይህ ሁሉ ነገር መሆን ሲጀምር ባያችሁ ጊዜ የእግዚአብሔር መንግሥት ልትመጣ መቃረብዋን ዕወቁ።

32 “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።

33 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም።”


ተግቶ ስለ መጠበቅ

34 ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በመብልና በመጠጥ ብዛት በስካርም በመባከንና ስለ ዓለማዊ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝል ተጠንቀቁ! አለበለዚያ ያ ቀን እንደ ወጥመድ በድንገት ይይዛችኋል።

35 ያ ቀን በምድር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ በድንገት ያጠምዳቸዋል።

36 ስለዚህ ከሚመጣው ክፉ ነገር ሁሉ ለማምለጥ ኀይል እንድታገኙና በሰው ልጅ ፊት ለመቆም እንድትችሉ እየጸለያችሁ ዘወትር ትጉ።”

37 ኢየሱስ በየቀኑ በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ ሲመሽ ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ላይ እየወጣ ያድር ነበር።

38 ሰዎቹ ሁሉ ኢየሱስን ለመስማት ጠዋት በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos