Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 62 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በእግዚአብሔር ጠባቂነት መተማመን

1 የሚያድነኝ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ፥ እግዚአብሔርን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።

2 ያለ እርሱ የሚጠብቀኝና የሚያድነኝ የለም፤ መከላከያዬም እርሱ ስለ ሆነ ከቶ አልናወጥም።

3 እንደ አረጀ ግድግዳና እንደ ተነቃነቀ አጥር ዐቅም ያነሰውን ሰው፥ ሁላችሁም በእርሱ ላይ አደጋ እየጣላችሁ። እስከ መቼ ስታጠቁት ትኖራላችሁ?

4 እነርሱ የሚፈልጉት ክብሩን ለመሻር ስለ ሆነ በእርሱ ላይ ሐሰት መናገርን ይወዳሉ፤ በአፋቸው ይመርቁታል፤ በልባቸው ግን ይረግሙታል።

5 እግዚአብሔርን ብቻ ጸጥ ብዬ እጠብቃለሁ፤ ተስፋዬም የሚመጣው ከእርሱ ነው።

6 የሚያድነኝ ኀያል አምባዬ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እርሱም እምነት የምጥልበት ምሽጌ ስለ ሆነ አልናወጥም።

7 መዳኔና ክብሬ የተገኘው ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ የመጠጊያዬ አምባና መጠለያዬ ነው።

8 ሕዝቦች ሆይ! ዘወትር በእግዚአብሔር ታመኑ፤ እርሱ መጠጊያችን ስለ ሆነ የልባችሁን ሐሳብ ሁሉ ለእርሱ አቅርቡ።

9 ተራ ሰዎች እንደ አየር ናቸው፤ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ተጨባጭነት እንደሌለው ምኞት ናቸው፤ ሁለቱ በሚዛን ላይ ቢቀመጡ ከነፋስ ሽውታ ይቀላሉ።

10 በብዝበዛ አትመኩ፤ በቀማችሁትም ነገር ለመክበር ተስፋ አታድርጉ፤ ሀብታችሁ ቢበዛ እንኳ በእርሱ አትተማመኑ።

11 እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናግሮአል፤ ኀይል የእግዚአብሔር መሆኑን ሁለት ጊዜ ሰምቼአለሁ።

12 ጌታ ሆይ! ለሁሉም እንደየሥራው ስለምትከፍል ዘለዓለማዊ ፍቅር ያንተ ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos