ዮሐንስ 4:10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኢየሱስም፣ “የእግዚአብሔርን ስጦታ ብታውቂና ውሃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ፣ አንቺው በጠየቅሽው፣ እርሱም የሕይወትን ውሃ በሰጠሽ ነበር” ሲል መለሰላት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ወሃ አጠጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ፥ አንቺ በለመንሽው ነበር፤ የሕይወትም ውሃ በሰጠሽ ነበር፤” አላት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ጌታችን ኢየሱስም፥ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ ብሎ የሚለምንሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂስ አንቺ ደግሞ በለመንሺው ነበር፤ እርሱም የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር” ብሎ መለሰላት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ኢየሱስ መልሶ፦ የእግዚአብሔርን ስጦታና፦ ወኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። |
እነሆ፥ እኔ በሲና ተራራ በአለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ አንተም አለቱን ምታው፤ ሕዝቡም የሚጠጡት ውሃ ከውስጡ ይፈልቃል፤” ሙሴም በእስራኤል አለቆች ፊት እንደዚሁ አደረገ።
አንቺ የአትክልት ቦታን እንደምታጠጣ ምንጭ ነሽ፤ የሕይወት ውሃም እንደሚገኝባት ጒድጓድ ነሽ፤ ከሊባኖስ ተራራ ሥር እንደሚፈልቅ ወንዝ ነሽ።
ለተመረጡት ሕዝቤ ውሃን ለመስጠት ወንዞች በበረሓ ጅረቶች በምድረ በዳ እንዲፈስሱ ባደረግሁ ጊዜ የምድር አራዊት እንኳ ሳይቀሩ ያከብሩኛል፤ ቀበሮዎችና ሰጎኖችም ያመሰግኑኛል።
“ለተጠማው ምድር ውሃን እሰጣለሁ፤ በደረቀውም ምድር ጅረቶች እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ መንፈሴን በልጆችህ ላይ አፈሳለሁ፤ በረከትንም ለልጅ ልጆችህ እሰጣለሁ።
መራብና መጠማትም አይደርስባቸውም፤ የሚያቃጥል ነፋስ ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም፤ ይህም የሚሆነው የሚራራላቸው እርሱ የውሃ ምንጭ ወደሚገኝበት ቦታ ስለሚመራቸው ነው።
እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል! ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል! እርሱም መሪ ይሆናል፤ ስሙም “ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ” ይባላል።
ሕዝቤ ሁለት ኃጢአት ሠርተዋል፤ ይኸውም የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንኩትን እኔን ትተውኛል፤ ውሃ መቋጠር የማይችሉ የተሸነቈሩ ጒድጓዶችን ለራሳቸው ቆፍረዋል።”
የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ለዳዊት ልጆችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከኃጢአታቸውና ከርኲሰታቸው የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።
በዚያን ቀን ከኢየሩሳሌም የሕይወት ውሃ ይፈልቃል፤ ከእርሱም እኩሌታው በምሥራቅ በኩል ወደ ሙት ባሕር፥ እኩሌታው በምዕራብ በኩል ወደ ሜዲቴራኒያን ባሕር ይፈስሳል፤ በበጋም ሆነ በክረምት ዓመቱን ሙሉ ሲፈስ ይኖራል።
እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ በሰማይ የሚኖር አባታችሁማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!”
እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።”
ከሰማይ የወረደው ሕይወትን የሚሰጥ እንጀራ እኔ ነኝ፤ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ሁሉ ለዘለዓለም ይኖራል፤ ለዓለም ሕይወት እንዲሆን እኔ የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።”
ጌታም እንዲህ አለው፦ “ቀጥተኛ ወደምትባለው መንገድ ሂድ፤ እዚያ በይሁዳ ቤት ሳውል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን በጸሎት ላይ ነው።”
እናንተን ግን እግዚአብሔር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ አደረገ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን ጥበባችን፥ ጽድቃችን፥ ቅድስናችንና ቤዛችን እንዲሆን አደረገው።
ሁሉም አንድ ዐይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ የጠጡትም ይከተላቸው ከነበረው ከዚያ ከመንፈሳዊ አለት የመነጨ ነበር፤ ያም አለት ራሱ ክርስቶስ ነበር።
እምነታቸውን የካዱትን ሰዎች ወደ ንስሓ መመለስ እንዴት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት ብርሃን በርቶላቸው ነበር፤ ሰማያዊውንም ስጦታ ቀምሰው ነበር፤ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ተካፋዮች ሆነው ነበር፤
የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣና እውነተኛውን አምላክ እንድናውቅ አስተዋይ ልቡና እንደ ሰጠን እናውቃለን በልጁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእርሱ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ኅብረት አለን። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛው አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው።
ከዚህም በኋላ እንዲህ አለኝ፤ “ተፈጸመ! አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ ለተጠማ ከሕይወት ውሃ ምንጭ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ እሰጠዋለሁ፤
መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና!” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውሃ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ ይጠጣ።