Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዮሐንስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኢየሱስና አንዲት ሳምራዊት ሴት

1 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርግና እንደሚያጠምቅ ፈሪሳውያን ሰሙ፤

2 ሆኖም ያጠምቁ የነበሩት የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንጂ እርሱ ራሱ አያጠምቅም ነበር።

3 ስለ እርሱ የተባለውን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ባወቀ ጊዜ ኢየሱስ የይሁዳን ምድር ትቶ ወደ ገሊላ ተመልሶ ሄደ።

4 ወደዚያም ሲሄድ በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት።

5 ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ወደምትገኝ፥ ሲካር ተብላ ወደምትጠራ የሰማርያ ከተማ መጣ።

6 በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጒድጓድ ነበረ፤ ኢየሱስ መንገድ ከመሄድ የተነሣ ስለ ደከመው በጒድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ነበረ።

7 በዚያን ጊዜ አንዲት የሰማርያ አገር ሴት ውሃ ልትቀዳ ወደ ጒድጓዱ መጣች፤ ኢየሱስም “ውሃ አጠጪኝ!” አላት።

8 በዚያን ወቅት ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበር።

9 ይህችም ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን፦ “አንተ ከአይሁድ ወገን ሆነህ እንዴት እኔን ሳምራዊቷን ‘ውሃ አጠጪኝ!’ ብለህ ትጠይቀኛለህ?” አለችው፤ ይህን ማለትዋ፥ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር ስምምነት ስላልነበራቸው ነው።

10 ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት።

11 እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ጌታ ሆይ! አንተ መቅጃ የለህም፤ ጒድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ታዲያ፥ የሕይወት ውሃ ከየት ታገኛለህ?

12 አንተ ይህን ጒድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱና ልጆቹ፥ ከብቶቹም ከዚህ ጒድጓድ ጠጥተዋል።”

13 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላት፤ “ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማዋል፤

14 እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።”

15 ሴትዮዋም “ጌታ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ውሃ እንዳይጠማኝና ወደዚህም ለመቅዳት እንዳልመጣ እባክህ እንዲህ ዐይነቱን ውሃ ስጠኝ!” አለችው።

16 ኢየሱስም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመለሺ” አላት።

17 ሴትዮዋም “ባል የለኝም” ስትል መለሰች፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላት፦ “ባል የለኝም ማለትሽ ልክ ነው፤

18 አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁንም ከአንቺ ጋር ያለው ሰው ባልሽ አይደለም፤ ስለዚህ እውነቱን ተናግረሻል።”

19 ሴትዮዋም እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ! አንተ ነቢይ እንደ ሆንክ አሁን ዐወቅሁ፤

20 አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ ሰገዱ፤ እናንተ ግን ‘ሰዎች ሊሰግዱ የሚገባቸው በኢየሩሳሌም ነው’ ትላላችሁ።”

21 ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፥ በዚህ ተራራ ላይ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ፤

22 እናንተ ለማታውቁት አምላክ ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን መዳን የሚመጣው ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው አምላክ እንሰግዳለን።

23 ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ፥ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ እንዲያውም አሁን መጥቶአል፤ አብም የሚፈልገው በዚህ መንገድ የሚሰግዱለትን ነው።

24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባቸዋል።”

25 ሴትዮዋም “ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።

26 ኢየሱስም “እነሆ! አሁን የማነጋግርሽ እኔ እርሱ ነኝ” አላት።

27 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ከሄዱበት ተመልሰው መጡ፤ ኢየሱስ ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተገረሙ፤ ይሁን እንጂ “ምን ትፈልጋለህ? ወይም ከእርስዋ ጋር ለምን ትነጋገራለህ?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም።

28 ከዚህ በኋላ ሴትዮዋ እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደችና ለሰዎቹ እንዲህ አለች፦

29 “የሠራሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑ እዩ! ምናልባት እርሱ መሲሕ ይሆንን?”

30 ሰዎቹም ከከተማ ወጥተው ወደ ኢየሱስ ሄዱ።

31 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን፦ “መምህር ሆይ! አንዳች ምግብ ብላ” ሲሉ ለመኑት።

32 እርሱ ግን፥ “እናንተ የማታውቁት እኔ የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው።

33 ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፥ “አንዳች ሰው ምግብ አምጥቶለት ይሆን?” ተባባሉ።

34 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና ሥራውንም መፈጸም ነው።

35 እናንተ ‘ገና አራት ወር ቀርቶታል፤ ከዚያም በኋላ መከር ይሆናል’ ትሉ የለምን? እኔ ግን ‘ቀና በሉና እርሻዎቹ ለመከር እንደ ደረሱ ተመልከቱ’ እላችኋለሁ።

36 የሚያጭድ ደመወዙን ይቀበላል፤ ለዘለዓለም ሕይወት የሚሆን ፍሬም ይሰበስባል፤ ስለዚህ የሚዘራውም፥ የሚያጭደውም አብረው ይደሰታሉ።

37 በዚህም ምክንያት ‘አንዱ ይዘራል፥ ሌላው ያጭዳል’ የተባለው አባባል እውነት ነው።

38 እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ፤ ሌሎች በሥራ ደከሙ፤ እናንተ ግን በድካማቸው ፍሬ ተጠቀማችሁ።”

39 ሴትዮዋ “የሠራሁትን ነገር ሁሉ ነገረኝ” ብላ በመሰከረችው መሠረት ከዚያ ከተማ ብዙዎቹ የሰማርያ ሰዎች አመኑ።

40 ስለዚህ የሰማርያ አገር ሰዎች ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲቈይ ለመኑት፤ እርሱም ሁለት ቀን እዚያ ቈየ።

41 በቃሉም ምክንያት ሌሎች ብዙ ሰዎችም በእርሱ አመኑ።

42 ሴትዮዋንም “ከእንግዲህ ወዲህ እርሱን የምናምነው አንቺ በነገርሽን ቃል ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ስለ ሰማንና በእርግጥ እርሱ የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ ስላወቅን ነው” አሉአት።


ኢየሱስ የሹሙን ልጅ እንደ ፈወሰ

43 ኢየሱስ በሰማርያ ሁለት ቀን ከቈየ በኋላ ወደ ገሊላ ሄደ።

44 እርሱ ራሱ “ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም” ብሎ ተናግሮ ነበር።

45 ነገር ግን ወደ ገሊላ በደረሰ ጊዜ የገሊላ ሰዎች በመልካም ሁኔታ ተቀበሉት፤ ይህም የሆነው ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በነበረበት ጊዜ እርሱ በዚያ ያደረገውን ሁሉ አይተው ስለ ነበር ነው።

46 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ውሃውን የወይን ጠጅ ወደ ለወጠባት በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ ቃና ከተማ እንደገና ተመለሰ፤ በዚያን ጊዜ በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት አንድ የቤተ መንግሥት ሹም ነበረ።

47 እርሱም ኢየሱስ ከይሁዳ ምድር ወደ ገሊላ መምጣቱን ሰምቶ ወደ እርሱ ሄደ፤ ወደ ቅፍርናሆም እንዲወርድና በጠና ታሞ ሊሞት የተቃረበውን ልጁን እንዲፈውስለት ኢየሱስን ለመነው።

48 ኢየሱስም “እናንተ ተአምራትና ድንቅ ነገር ካላያችሁ በቀር ምንም አታምኑም!” አለው።

49 ሹሙም “ጌታ ሆይ! ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ ቶሎ ውረድ” አለው።

50 ኢየሱስም “ወደ ቤትህ ሂድ! ልጅህ በሕይወት ይኖራል” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ወደ ቤቱ ሄደ።

51 ሲሄድም አገልጋዮቹ በመንገድ አገኙትና “ልጅህ ድኖአል” ብለው ነገሩት።

52 እርሱም ልጁ በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው። እነርሱም “ትናንትና በሰባት ሰዓት ላይ ትኲሳቱ ለቀቀው” አሉት።

53 አባትየውም ኢየሱስ “ልጅህ በሕይወት ይኖራል” ያለው በዚያኑ ሰዓት እንደ ሆነ ዐወቀ፤ ስለዚህ ከዚያን ቀን ጀምሮ እርሱና ቤተ ሰቡ ሁሉ በኢየሱስ አመኑ።

54 ይህ ተአምር ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛው ተአምር ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos