ኤርምያስ 48:11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከዕቃ ወደ ዕቃ ሳይገለባበጥ ከአተላው ጋር አብሮ የቈየ የወይን ጠጅ ጣዕሙ እንዳለ ይቈያል፤ መዓዛውም አይለወጥም፤ እንደዚሁም የሞአብ ሕዝብ አገራቸው ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሳይታወኩ ኖረዋል፤ ተማርከውም አይታወቁም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም “ሞዓብ በአንቡላው ላይ እንዳረፈ የወይን ጠጅ፣ ከልጅነት ጀምሮ የተረጋጋ ነበረ፤ ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤ በምርኮም አልተወሰደም፤ ቃናው እንዳለ ነው፤ መዐዛውም አልተለወጠም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሞዓብ ከብላቴንነቱ ጀምሮ ተረጋግቷል፥ በአምቡላውም ላይ ዐርፎአል፥ ከዕቃም ወደ ዕቃ አልተንቈረቈረም፥ ወደ ምርኮም አልሄደም፤ ስለዚህ ቃናው በእርሱ ውስጥ ቀርቶአል፥ መዓዛውም አልተለወጠም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ሞአብ ከልጅነቷ ጀምራ ዐረፈች፤ በክብርዋም ቅምጥል ነበረች፤ ወይንዋም ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤ ወደ ምርኮም አልሄደችም፤ ስለዚህ ቃናው በእርስዋ ውስጥ ቀርቶአል፤ መዓዛዋም አልተለወጠም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሞዓብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ቅምጥል ነበረ፥ በአምቡላውም ላይ ዐርፎአል፥ ከዕቃውም ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፥ ወደ ምርኮም አልሄደም፥ ስለዚህ ቃናው በእርሱ ውስጥ ቀርቶአል፥ መዓዛውም አልተለወጠም። |
የይሁዳ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ “የሞአብ ሕዝብ ምን ያኽል ኩራተኛ መሆኑን፥ ትዕቢተኛነቱን፥ ዕብሪተኛነቱንና ንቀቱን ሰምተናል፤ ነገር ግን ፉከራው ሁሉ ከንቱ ነው።”
የሠራዊት አምላክ በዚህች በጽዮን ተራራ ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ታላቅ ግብዣ ያዘጋጃል፤ በግብዣውም ላይ ምርጥ የወይን ጠጅና፥ የተሟላ ምግብ ይዘጋጃል።
በብልጽግና በምትኖሩበት ጊዜ እግዚአብሔር ተናገራችሁ፤ እናንተ ግን ማዳመጥ እምቢ አላችሁ፤ ከመጀመሪያ ጀምሮ የምታደርጉት ይህንኑ ነው። እግዚአብሔርንም መታዘዝ እምቢ አላችሁ።
አንድ ሰው የወይን ጠጅን ከአንድ ዕቃ ወደ ሌላ ዕቃ ገልብጦ ባዶውን ዕቃ እንደሚሰብር፥ እኔም ሞአብን የሚያወድምና ሕዝብዋን የሚያፈልስ ሰው የምልክበት ጊዜ በእርግጥ ተቃርቦአል።
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን በዘበዘ አደቀቃትም እንደ ባዶ ዕቃም አደረጋት፤ እንደ ዘንዶ ሕዝብዋን ዋጠ፤ ምርጥ ምርጡን ወስዶ የቀሩትን እንደሚተፋ ምግብ ጣላቸው።
ነነዌ ተደመሰሰች፤ ፈራርሳም ወደመች፤ የሰው ልብ በፍርሃት ቀለጠ፤ ጉልበቶችም ተብረከረኩ፤ የሰው ሁሉ ወገብ ተንቀጠቀጠ። የሰውም ሁሉ ፊት ገረጣ፤
“በዚያን ቀን መብራት ይዤ ኢየሩሳሌምን እፈትሻለሁ፤ በመንደላቀቅ ኑሮ በአተላ ውስጥ አቅርሮ እንደ ቀረ የወይን ጠጅ የሆኑትንና ‘እግዚአብሔር በጎም ሆነ ክፉ ነገር አያደርግም’ የሚሉትን እቀጣለሁ።
ሰላም አግኝተው በጸጥታ በሚኖሩ በአሕዛብ መንግሥታት ላይ እጅግ ተቈጥቼአለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ሕዝቤን ከመቅጣት መለስ ባልኩበት ጊዜ እነዚያ የአሕዛብ መንግሥታት ሕዝቤን ከተጠበቀው በላይ አሠቃይተዋል።