ናሆም 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየነነዌ አወዳደቅ 1 ነነዌ ሆይ! አደጋ ጣይ መጥቶብሻል! ስለዚህ ምሽጎችሽን አጠናክሪ! አውራ መንገዱን ሁሉ ጠብቂ! ወገብሽን ታጠቂ! ኀይልሽንም ሁሉ አጠናክሪ! 2 አጥፊዎች እነርሱንና ሀብታቸውን ቢያወድሙም እንኳ እግዚአብሔር የያዕቆብ ልጆች የሆኑትን የእስራኤልን ክብር ይመልሳል። 3 ወታደሮች ቀያይ ጋሻዎችን አንግበዋል፤ ወታደሮቹ ሐምራዊ ልብስ ለብሰዋል፤ እርሱ ሲያሰልፋቸው የሠረገላዎቹ ብረት ያንጸባርቃል፤ ፈረሰኞቹ በፈረስ ላይ ሆነው ይቊነጠነጣሉ። 4 ሠረገሎቹ በከፍተኛ ፍጥነት በመንገዶች ይሽቀዳደማሉ፤ በአደባባዩም ላይ ወዲያና ወዲህ ይጣደፋሉ፤ የሚንቦገቦግ ችቦም ይመስላሉ፤ እንደ መብረቅም ይወረወራሉ። 5 እርሱ የጦር ሹማምንቱን ይጠራል፤ እነርሱም እየተደናቀፉ ወደፊት ይመጣሉ፤ የጠላት ወታደሮች እየሮጡ ወደ ከተማይቱ ቅጽር ይወጣሉ፤ የሚወረወርባቸውንም ፍላጻ በትልቁ ጋሻቸው ይከላከላሉ። 6 በወንዙ በኩል ያሉት የከተማይቱ ቅጽር በሮች ወለል ብለው ተከፈቱ፤ ቤተ መንግሥቱም በሽብር ተሞላ። 7 ነነዌ ተዋረደች፤ ንግሥቲቱ ተማርካ ተወሰደች፤ ሴቶች አገልጋዮችዋ የርግብ ድምፅ የመሰለ የሐዘን ድምፅ ያሰማሉ፤ ደረታቸውንም እየመቱ ያለቅሳሉ። 8 ነነዌ ውሃዋ እንደሚፈስ ኩሬ ናት፤ ሕዝብዋም እንደሚፈሰው ውሃ ከከተማይቱ ወጥቶ ሲሄድ “ቁሙ! ቁሙ!” የሚለውን ሰው ዞር ብሎ አያይም። 9 የከተማይቱ ሀብት መጨረሻ የለውም፤ የከበሩ ድንጋዮቹም የተትረፈረፉ ናቸው፤ ስለዚህ ሄዳችሁ ብሩንና ወርቁን በዝብዛችሁ ውሰዱ። 10 ነነዌ ተደመሰሰች፤ ፈራርሳም ወደመች፤ የሰው ልብ በፍርሃት ቀለጠ፤ ጉልበቶችም ተብረከረኩ፤ የሰው ሁሉ ወገብ ተንቀጠቀጠ። የሰውም ሁሉ ፊት ገረጣ፤ 11 አንበሶች የሚኖሩበትን፥ የአንበሶች ደቦሎች የሚመገቡበትን፥ ወንድና ሴት አንበሶች ከግልገሎቻቸው ጋር ያለ ስጋት የሚዝናኑበትን መስክ ትመስል የነበረችው፥ ያቺ ከተማ አሁን የት አለች? 12 አንበሳ ለግልገሎቹ የሚበቃቸውን ያኽል ዐድኖ አመጣ፤ ለእንስቲቱ አንበሳም የምትመገበውን ገድሎ አመጣላት፤ ዋሻውን በታደኑ እንስሶች ጒድጓዱንም በተቦጫጨቀ ሥጋ ሞላ። 13 ነነዌ ሆይ! በአንቺ ላይ ተነሥቼአለሁ ይላል የሠራዊት አምላክ፤ ሠረገሎችሽንም አቃጥላለሁ፤ ደቦሎችሽንም ሰይፍ ይበላቸዋል፤ በምድር ላይ በአንቺ ተጠቂ የሚሆን እንዳይኖር አደርጋለሁ፤ የመልእክተኞችሽም ድምፅ ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም። |