ኤርምያስ 21:2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከነሠራዊቱ ከተማይቱን ለመውጋት በመክበብ ላይ ይገኛል፤ ስለዚህ ምናልባት በረድኤት ከእኛ ጋር ሆኖ ድንቅ ሥራውን በመግለጥ ናቡከደነፆርን እንዲመለስ ያደርግልን እንደ ሆነ እግዚአብሔርን ጠይቅልን።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሊወጋን ስለ ሆነ፣ እባክህን ፈጥነህ፣ እግዚአብሔርን ጠይቅልን፤ ምናልባት ንጉሡ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ቀድሞው ታምራት ያደርግልን ይሆናል” ብለው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፥ እባክህ፥ ጌታን ጠይቅ፤ ምናልባትም ጌታ ለእኛ እንደ ተአምራቱ ሁሉ አድርጐ ከእኛ እንዲመለስ ያደርገዋልና።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋን ዘንድ መጥቶአልና ከእኛ ይመለስ ዘንድ፥ ምናልባትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ እንደ ሆነ ስለ እኛ፥ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይህም የሆነው ንጉሡ ሴዴቅያስ፦ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅ፥ ከእኛም ይመለስ ዘንድ ምናልባት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ ይሆናል ብሎ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስ ወደ ኤርምያስ በላከ ጊዜ ነው። |
ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ቴስቢያዊውን ኤልያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “ተነሥተህ የሰማርያ ንጉሥ አካዝያስ የላካቸውን መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣ፤ እንዲህም ብለህ ንገራቸው፤ ‘የዔክሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱት፥ በእስራኤል ዘንድ አምላክ የለም ብላችሁ በማሰብ ነውን?’
የአሦር ንጉሠ ነገሥት በባቢሎን፥ ኩታ፥ ዓዋ፥ ሐማትና ሰፋርዋይም ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብ አምጥቶ ተሰደው በሄዱት በእስራኤላውያን እግር በመተካት በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም እነዚህን ከተሞች ወርሰው በዚያ መኖር ጀመሩ።
እግዚአብሔርም መልአክን ልኮ የአሦርን ወታደሮችና የጦር መኰንኖች እንዲገደሉ አደረገ፤ ስለዚህም የአሦር ንጉሠ ነገሥት ተዋርዶ ወደ አገሩ ተመለሰ፤ አንድ ቀን በአምላኩ መስገጃ ስፍራ በነበረበት ወቅት የገዛ ልጆቹ በሰይፍ ገደሉት።
በረዶውና ነጐድጓዱ እጅግ ስለ በዛብን ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ በእርግጥ እለቃችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እዚህ የምትቈዩበት ጊዜ አይኖርም።”
ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “በእርግጥ ለመልካም ዓላማ እታደግሃለሁ፤ በችግርና በመከራ ጊዜ ጠላቶችህ አንተን እንዲለማመጡ አደርጋለሁ።
“እነሆ ባቢሎናውያን ከተማይቱን ለመያዝ ዐፈር ቈልለው ዙሪያዋን በመክበብ ላይ ናቸው፤ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር ከተማይቱ በእነርሱ እጅ እንድትወድቅ ያደርጓታል፤ እነሆ አንተ የተናገርከው ሁሉ መድረሱን ታያለህ፤
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ በግዛቱ ሥር ባሉት መንግሥታትና ሕዝቦች ጭምር እየተረዳ በኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ላይ የጦርነት አደጋ በሚጥልበት ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።
ዘግየት ብሎም ንጉሥ ሴዴቅያስ መልእክተኛ ልኮ አስወሰደኝና በቤተ መንግሥቱ በግል ሲያነጋግረኝ “ከእግዚአብሔር የተነገረህ የትንቢት ቃል አለን?” ብሎ ጠየቀኝ። “አዎ፥ አለ!” ብዬ ንግግሬን በመቀጠል “አንተ ለባቢሎን ንጉሥ ተላልፈህ ትሰጣለህ” አልኩት።
ንጉሥ ሴዴቅያስ የሼሌምያን ልጅ የሁካልንና የማዕያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እኔ ወደ ኤርምያስ ልኮ “ስለ ሕዝባችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ” ብለው እንዲጠይቁኝ አደረገ።
አንዱ መቅሠፍት ሌላውን ያስከትላል፤ አንዱ ወሬም ሌላውን ወሬ ተከታትሎ ይመጣል፤ ነቢያት ያዩትን ራእይ እንዲነግሩአችሁ ትለምኑአቸዋላችሁ፤ ካህናት ሕዝቡን የሚያስተምሩት ሕግ፥ ሽማግሌዎችም ለሕዝቡ የሚሰጡት ምክር ጠፋባቸው።
ስለዚህም እነርሱ “ሌላ የቀረ ይኖር ይሆን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም “ሳኦል እነሆ በዕቃ መካከል ተደብቆ ይገኛል” ሲል መለሰላቸው።
ሳሙኤልም ሳኦልን “ዕረፍት የምትነሣኝ ስለምንድን ነው? ስለምንስ ከመቃብር እንድነሣ አስጠራኸኝ?” አለው። ሳኦልም “እነሆ፥ እኔ በታላቅ ችግር ላይ ነኝ! ፍልስጥኤማውያን ከእኔ ጋር ጦርነት በማድረግ ላይ ናቸው፤ እግዚአብሔርም እኔን ትቶኛል፤ በነቢይም ሆነ በሕልም መልስ ሊሰጠኝ አልፈለገም፤ ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ትነግረኝ ዘንድ እንድትነሣ አስጠራሁህ” ሲል መለሰ።
ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባው እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔር ግን በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አማካይነት መልስ እንዲሰጠው አልፈቀደም።