Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ዘፀአት 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሠ. የእንስሶች እልቂት

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ንጉሡ ሄደህ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል በለው፦ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

2 ዳግመኛ እምቢ ብትል ግን፥

3 የእግዚአብሔር እጅ በመስክ የሚገኘውን መንጋህን ማለት ፈረሶችህን፥ አህዮችህን፥ ግመሎችህን፥ የቀንድ ከብቶችህን፥ በጎችህንና ፍየሎችህን በታላቅ መቅሠፍት ይመታል።

4 እግዚአብሔር ግን በእስራኤላውያንና በግብጻውያን እንስሶች መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ከእስራኤላውያን እንስሶች አንድ እንኳ አይሞትም።

5 እግዚአብሔር ይህን ነገር ነገ አደርጋለሁ ብሎ ጊዜውን ወሰነ።’ ”

6 እግዚአብሔርም በተናገረው መሠረት በማግስቱ ይህንኑ አደረገ፤ የግብጻውያን እንስሶች ሁሉ አለቁ፤ ነገር ግን ከእስራኤላውያን እንስሶች አንድ እንኳ አልሞተም።

7 ንጉሡ የሆነውን ሁሉ ለማጣራት ሰዎችን በላከ ጊዜ ከእስራኤላውያን እንስሶች አንድ እንኳ አለመሞቱን ተረዳ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ልቡን ስላደነደነ ሕዝቡን አለቀቀም።


ረ. ብጉንጅ የመሰለ ብርቱ ቊስል

8 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “በእፍኛችሁ እየዘገናችሁ ከምድጃ ጥቂት ዐመድ ውሰዱ፤ እርሱንም ሙሴ በንጉሡ ፊት ወደ አየር ይበትነው፤

9 እርሱም እንደ ደቃቅ ትቢያ ሆኖ በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ በሚሠራጭበት ጊዜ በሕዝብና በእንስሶቹ ላይ አሠቃቂ የሆነ ብርቱ ቊስል ያመጣል።”

10 እነርሱም ጥቂት ዐመድ ከምድጃ ወስደው በንጉሡ ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ አየር በበተነው ጊዜ ሕዝቡና እንስሶቹ በብርቱ ቊስል ተመቱ።

11 እንደማንኛውም ግብጻዊ እነርሱም ቈስለው ስለ ነበረ በዚያን ጊዜ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቅረብ አልቻሉም፤

12 ነገር ግን አሁንም እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ በማደንደን እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሙሴ እንደ ተናገረ ንጉሡ ሙሴንና አሮንን አላደመጣቸውም።


ሰ. የበረዶ መዝነብ

13 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ነገ ጠዋት በማለዳ ወደ ንጉሡ ሄደህ በፊቱ ቆመህ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል’ ብለህ ንገረው፤ ‘ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤

14 ነገር ግን እምቢ ብትል፥ በዓለም ላይ እኔን የመሰለ ሌላ አምላክ እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተን ራስህን፥ መኳንንትህንና ሕዝብህን በመቅሠፍቴ ኀይል አሁኑኑ እቀጣለሁ።

15 አንተንና ሕዝብህን በመቅሠፍት ለመምታት የኀይል ክንዴን አንሥቼ ቢሆን ኖሮ እስከ አሁን ከምድር በተወገዳችሁ ነበር።

16 ነገር ግን ስሜ በዓለም ሁሉ ይጠራ ዘንድ ኀይሌን ላሳይህ ስለ ፈለግኹ በሕይወት እንድትቈይ አድርጌአለሁ።

17 አንተ እስከ አሁንም በሕዝቤ ላይ ታብየሃል፤ እንዲሄዱም አልፈቀድክላቸውም።

18 እነሆ፥ ነገ በዚህ ጊዜ በግብጽ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የበረዶ ዝናብ አመጣለሁ፤

19 አሁንም በመስክ የተሰማሩት እንስሶችህና በዚያ ያለው ንብረትህ ሁሉ ወደ መጠለያ እንዲጠጋ ትእዛዝ ስጥ፤ ወደ ቤት ያልገቡ ሰዎችም ሆኑ እንስሶች ቢኖሩ ግን በበረዶው ስለሚመቱ ሁሉም ያልቃሉ።’ ”

20 ከንጉሡ ባለሟሎች አንዳንዶቹ እግዚአብሔር ስለ ተናገረው ነገር በፍርሃት ተጨነቁ፤ ስለዚህም አገልጋዮቻቸውና እንስሶቻቸው ወደ ቤት ተሰብስበው እንዲጠለሉ አደረጉ።

21 የቀሩት ግን እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል ችላ በማለት አገልጋዮቻቸውንና እንስሶቻቸውን በሜዳ ተዉ።

22 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በረዶም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ይዘንባል፤ ሕዝቡን፥ እንስሶቹ በእርሻ ያለውን ተክል ሁሉ ይመታል” አለው።

23 ስለዚህ ሙሴ በትሩን አንሥቶ ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም ነጐድጓድና በረዶ መብረቅም ወደ ምድር አወረደ፤ በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር በግብጽ ምድር ላይ በረዶን አዘነበ።

24 እግዚአብሔር በዚህና በዚያ ከሚራወጥ የመብረቅ ብልጭልጭታ ጋር ከባድ የበረዶ ዝናብ አወረደ፤ ይህም ዐይነቱ የበረዶ ዝናብ በግብጽ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነበር።

25 በረዶው በግብጽ ምድር ሁሉ በሜዳ የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ሕዝቡንና እንስሶቹን ጭምር ጨፈጨፈ፤ በሜዳ ላይ ያለውን አትክልት ሁሉ መታ፤ ዛፎችንም ሁሉ ሰባበረ።

26 እስራኤላውያን በሚኖሩባት በጌሴም ምድር ብቻ በረዶ አልነበረም።

27 ንጉሡም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ በድዬአለሁ፤ እግዚአብሔር እውነተኛ ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን በደለኞች ነን።

28 በረዶውና ነጐድጓዱ እጅግ ስለ በዛብን ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ በእርግጥ እለቃችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እዚህ የምትቈዩበት ጊዜ አይኖርም።”

29 ሙሴም ንጉሡን እንዲህ አለው፤ “ከከተማው እንደ ወጣሁ እጄን ዘርግቼ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነጐድጓዱም ይቆማል፤ በረዶም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም፤ በዚህ ዐይነት አንተም ምድር የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቃለህ።

30 ነገር ግን አንተና መኳንንትህ ገና እግዚአብሔር አምላክን የማትፈሩ መሆናችሁን ዐውቃለሁ።”

31 ገብስ ገና እሸት፥ ተልባውም ገና በማበብ ላይ ስለ ነበር አንድም ሳይቀር በሙሉ ተበላሸ።

32 ስንዴውና አጃው ግን የሚደርሱት ዘግየት ብለው ስለ ነበር ከመበላሸት ድነዋል።

33 ሙሴ ከንጉሡ ፊት በመውጣት ከከተማው ውጪ ሄደ፤ እጁንም ዘርግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ዝናቡም በአንድ ጊዜ ቆመ።

34 ንጉሡ ግን ዝናቡ፥ በረዶውና ነጐድጓዱ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ እርሱና መኳንንቱ ልባቸውን በማደንደን እንደገና ኃጢአት ሠሩ።

35 እግዚአብሔር አስቀድሞ በሙሴ አማካይነት ተናግሮ እንደ ነበረ ንጉሡ ልቡን አደንድኖ እስራኤላውያንን አለቀቀም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos