ኤርምያስ 37 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሴዴቅያስ ለኤርምያስ ያቀረበው ጥያቄ 1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የኢዮስያስን ልጅ ሴዴቅያስን የኢዮአቄም ልጅ በነበረው በኢኮንያን ምትክ በይሁዳ ላይ አነገሠው። 2 ሴዴቅያስም ሆነ መኳንንቱ ወይም ሕዝቡ እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ አማካይነት ለተናገረው ቃል ታዛዦች አልሆኑም። 3 ንጉሥ ሴዴቅያስ የሼሌምያን ልጅ የሁካልንና የማዕያን ልጅ ካህኑን ሶፎንያስን ወደ እኔ ወደ ኤርምያስ ልኮ “ስለ ሕዝባችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ” ብለው እንዲጠይቁኝ አደረገ። 4 እኔም ገና ወደ እስር ቤት አልገባሁም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በሕዝቡ ፊት በነጻ እመላለስ ነበር። 5 በዚያን ጊዜ የባቢሎን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከበበ፤ ነገር ግን የግብጽ ሠራዊት ድንበሩን አልፎ መምጣቱን በሰማ ጊዜ ወደ ኋላው አፈገፈገ። 6-7 ከዚህ በኋላ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሴዴቅያስ በመልእክተኞቹ አማካይነት እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፦ “እነሆ አንተን ለመርዳት መጥቶ የነበረው የግብጽ ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ በመመለስ ላይ ነው። 8 ከዚያ በኋላ ባቢሎናውያን ተመልሰው ይመጣሉ፤ አደጋም ጥለው ከተማይቱን ይይዛሉ፤ በእሳትም ያቃጥሉአታል፤ 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ባቢሎናውያን ተመልሰው ይሄዳሉ’ ብላችሁ ራሳችሁን አታታሉ፤ እነርሱ ተመልሰው አይሄዱም። 10 መላውን የባቢሎን ሠራዊት ድል ብትነሡ እንኳ ከእነርሱ ተርፈው በድንኳን ያረፉ ቊስለኞች እንደገና በማንሰራራት ተነሥተው ከተማይቱን በእሳት አቃጥለው ያወድሟታል።” ኤርምያስ ተይዞ መታሰሩ 11 የግብጽ ሠራዊት መቃረቡ እንደ ተሰማ የባቢሎን ሠራዊት ወደ ኋላ አፈግፍጎ ነበር፤ 12 እኔም ከቤተሰቤ የሚደርሰኝን የርስት ክፍያ ለመቀበል ወደ ብንያም ግዛት ለመሄድ ከኢየሩሳሌም ተነሣሁ። 13 ነገር ግን ከብንያም ቅጽር በር እንደ ደረስኩ የዘብ ጠባቂዎች አለቃ የሆነው ስሙ ዪሪያ ተብሎ የሚጠራ የሐናንያ የልጅ ልጅ የሆነው የሼሌምያ ልጅ “ከድተህ ወደ ባቢሎናውያን ልትሄድ ነው!” ብሎ አስቆመኝ። 14 እኔም “አንተ እንደምትለው እኔ ከድቼ የምሄድ ሰው አይደለሁም!” ብዬ መለስኩለት፤ ዪሪያ ግን ሊያዳምጠኝ አልፈለገም፤ ይልቁንም አስሮ ወደ ባለ ሥልጣኖች ወሰደኝ፤ 15 እነርሱም በብርቱ ተቈጥተው ካስደበደቡኝ በኋላ የእስር ቤት እንዲሆን አድርገውት ወደነበረው ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት ውስጥ አስገብተው ዘጉብኝ፤ 16 በዚያም ምድር ቤት ውስጥ በሚገኝ ክፍል ለብዙ ጊዜ ቈየሁ። 17 ዘግየት ብሎም ንጉሥ ሴዴቅያስ መልእክተኛ ልኮ አስወሰደኝና በቤተ መንግሥቱ በግል ሲያነጋግረኝ “ከእግዚአብሔር የተነገረህ የትንቢት ቃል አለን?” ብሎ ጠየቀኝ። “አዎ፥ አለ!” ብዬ ንግግሬን በመቀጠል “አንተ ለባቢሎን ንጉሥ ተላልፈህ ትሰጣለህ” አልኩት። 18 ከዚያም በኋላ እንዲህ ብዬ ጠየቅሁት፦ “እስር ቤት ታስገባኝ ዘንድ በአንተ፥ በመኳንንትህና በዚህ ሕዝብ ላይ የፈጸምኩት ወንጀል ምንድነው? 19 ለመሆኑ ‘የባቢሎን ንጉሥ በአንተም ሆነ በአገርህ ላይ አደጋ አይጥልም’ ብለው የነገሩህ ነቢያትህ አሁን የት አሉ? 20 ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! እንድታዳምጠኝና የምጠይቅህን እንድትፈጽምልኝ እለምንሃለሁ፤ ይኸውም እስር ቤት ወደ ሆነው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ፤ ወደዚያ ከመለስከኝ በእርግጥ እሞታለሁ።” 21 ስለዚህም ንጉሥ ሴዴቅያስ በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ እንዲዘጋብኝ አዘዘ፤ እኔም በዚያ ቈየሁ፤ ዳቦ ከከተማይቱ ጨርሶ እስከ ጠፋም ድረስ ከዳቦ መጋገሪያዎች አንድ ዳቦ በየቀኑ ይሰጠኝ ነበር። |