Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ለመውጋት የጦር ሠራዊታቸውን ሰበሰቡ፤ አኪሽም ዳዊትን “አንተና ተከታዮችህ ከእኔ ጐን ተሰልፋችሁ መዋጋት እንደሚገባችሁ በእርግጥ ዕወቅ” አለው።

2 ዳዊትም “እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ የማደርገውንም አንተ ራስህ ማየት ትችላለህ” ሲል መለሰለት። አኪሽም “መልካም ነው! እኔ አንተን ለዘለቄታ የራሴ የክብር ዘብ አደርግሃለሁ!” አለው።


ሳኦል ከሙታን መናፍስት ጠሪ ምክር መጠየቁ

3 እነሆ፥ ሳሙኤል ከሞተ ቈየት ብሎአል፤ እስራኤላውያንም ሁሉ ለእርሱ በማዘን አልቅሰው በሚኖርባት በራማ ቀብረውታል፤ ቀደም ሲል ሳኦል ጠንቋዮችንና ሙታን ጠሪዎችን ከእስራኤል ምድር እንዲባረሩ አስገድዶአቸው ነበር።

4 የፍልስጥኤም ወታደሮች ተሰልፈው መጥተው በሹኔም ከተማ አጠገብ ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤላውያንን አሰልፎ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ሰፈረ፤

5 ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ብዛት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም ተሸበረ፤

6 ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባው እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔር ግን በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አማካይነት መልስ እንዲሰጠው አልፈቀደም።

7 ከዚህ በኋላ ሳኦል “ሙታን ጠሪ የሆነች አንዲት ሴት ፈልጉልኝ፤ እኔም ሄጄ ምክር እጠይቃታለሁ” ሲል ባለሟሎቹን አዘዘ። እነርሱም “አንዲት ዔንዶራዊት አለች” ሲሉ መለሱለት።

8 ሳኦልም ልብሱን ለውጦ ማንነቱ እንዳይታወቅ በማድረግ በሌሊት ሁለት ሰዎች አስከትሎ ሴትዮዋን ለማየት ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ “መናፍስትን ጠይቀሽ ወደ ፊት ስለሚሆነው ነገር አስረጂኝ፤ ስሙንም የምጠራልሽን ሰው አስነሽልኝ” አላት።

9 ሴትዮዋም “ንጉሥ ሳኦል ያደረገውን ነገር ሁሉ ታውቃለህ፤ እርሱ እኮ ጠንቋዮችንና ሙታን ጠሪዎችን ከእስራኤል ምድር አጥፍቶአቸዋል፤ ታዲያ አንተ እኔን አጥምደህ ልታስገድለኝ የምትፈልገው ስለምንድን ነው?” ስትል መለሰችለት።

10 ከዚያም በኋላ ሳኦል “በዚህ ነገር ምንም ዐይነት ቅጣት እንደማይደርስብሽ በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ቃል እገባልሻለሁ” አላት።

11 “ታዲያ ማንን ላስነሣልህ?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “ሳሙኤልን አስነሽልኝ” አላት።

12 እርስዋም ሳሙኤልን ባየችው ጊዜ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ በመጮኽ “ስለምን አታለልከኝ? አንተ ንጉሥ ሳኦል ነህ!” አለችው።

13 ንጉሡም “አይዞሽ አትፍሪ! ይልቅስ የምታዪው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም “እኔ አንድ መለኮታዊ ግርማ ያለው ከመቃብር ሲወጣ እያየሁ ነኝ” አለችው።

14 እርሱም “መልኩ ምንን ይመስላል?” ሲል ጠየቃት። እርስዋም “እነሆ፥ ካባ የለበሰ አንድ ሽማግሌ ሰው እየተነሣ ነው” ስትል መለሰችለት። ሳኦልም ያ ሳሙኤል መሆኑን ዐውቆ ስለ ክብሩ በመሬት ላይ ለጥ ብሎ እጅ ነሣ።

15 ሳሙኤልም ሳኦልን “ዕረፍት የምትነሣኝ ስለምንድን ነው? ስለምንስ ከመቃብር እንድነሣ አስጠራኸኝ?” አለው። ሳኦልም “እነሆ፥ እኔ በታላቅ ችግር ላይ ነኝ! ፍልስጥኤማውያን ከእኔ ጋር ጦርነት በማድረግ ላይ ናቸው፤ እግዚአብሔርም እኔን ትቶኛል፤ በነቢይም ሆነ በሕልም መልስ ሊሰጠኝ አልፈለገም፤ ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ትነግረኝ ዘንድ እንድትነሣ አስጠራሁህ” ሲል መለሰ።

16 ሳሙኤልም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር ተለይቶህ ጠላትህ ከሆነ በኋላ እኔን ስለምን ታስጠራኛለህ?

17 እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት የነገረህን ሁሉ እየፈጸመ ነው፤ መንግሥቱንም ከአንተ እጅ ወስዶ ለጐረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል፤

18 አንተ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ ሆነህ አልተገኘህም፤ ዐማሌቃውያንና የእነርሱ የሆነውንም ሁሉ አልደመሰስክም፤ እንግዲህ እግዚአብሔር አሁን ይህን ሁሉ የሚያደርግብህ በዚህ ምክንያት ነው።

19 ስለዚህ እርሱ አንተንና እስራኤልን ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ ነገ አንተና ልጆችህ እኔ ወዳለሁበት ቦታ ትመጣላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ሠራዊት ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።”

20 ሳኦልም ሳሙኤል በተናገረው ቃል ደንግጦ በመዝለፍለፍ ወደቀ፤ በመሬት ላይም ተዘረረ፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ እህል ስላልቀመሰ ድካም ተሰምቶት ነበር።

21 ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጥታ ሲንቀጠቀጥ ስላየችው እንዲህ አለችው፦ “እኔ አገልጋይህ የአንተን ቃል ሰምቼ ሕይወቴን እስከ ማሳለፍ ደርሼአለሁ፤ ያልከኝንም ነገር አዳመጥኩ፤

22 አንተ ደግሞ አሁን የእኔን የአገልጋይህን ቃል ስማ፤ ምግብ ላዘጋጅልህና ተመገብ መንገድህንም በርትተህ መሄድ ትችላለህ።”

23 ሳኦል “ምንም ነገር አልቀምስም” ብሎ እምቢ አለ፤ ይሁን እንጂ ባለሟሎቹም እንዲመገብ አበረታቱት፤ በመጨረሻም “እሺ” ብሎ ከወደቀበት መሬት በመነሣት አልጋ ላይ ተቀመጠ፤

24 ሴትዮዋም የሰባ ጥጃ ነበራት እሱንም በፍጥነት ዐረደች፤ ጥቂት ዱቄትም ወስዳ በማቡካት እርሾ ያልነካው ቂጣ ጋገረች።

25 ምግቡንም ለሳኦልና ለባለሟሎቹ አቅርባላቸው ተመገቡ፤ በዚያኑም ምሽት ከዚያ ተነሥተው ሄዱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos