Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ሳሙኤል የወይራ ዘይት መያዣውን ቀንድ ወስዶ በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው፤ ሳመውም። ከዚያም በኋላ “እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን ቀባህ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነግሠህ በዙሪያቸው ካሉ ጠላቶች ታድናቸዋለህ እግዚአብሔር በርስቱ ላይ የሾመህ ለመሆኑ ይህ ማስረጃ ነው፤

2 ዛሬ ከእኔ ተለይተህ በምትሄድበት ጊዜ፥ በብንያም ግዛት በሚገኘው ጼልጻሕ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነርሱም ስትፈልጋቸው የነበሩ አህዮች መገኘታቸውንና አባትህም ስለ እነርሱ ማሰቡን ትቶ ስለ አንተ በመጨነቅ ‘እንግዲህ ስለ ልጄ ምን ላድርግ’ እያለ በመጠየቅ ላይ መሆኑን ይነግሩሃል።

3 ከዚያም አልፈህ በታቦር ወደሚገኘው ወደ አንድ ትልቅ ዛፍ ትደርሳለህ፤ እዚያም ወደ ቤትኤል ወደ እግዚአብሔር የሚሄዱ ሦስት ሰዎችን ታገኛለህ፤ ከእነርሱ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶችን እየሳበ የሚሄድ ሲሆን ሁለተኛው ሰው ሦስት ኅብስት የተሸከመ ነው፤ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ የተሸከመ ይሆናል፤

4 እነርሱም ሰላምታ ከሰጡህ በኋላ ከኅብስቶቹ ሁለቱን ይሰጡሃል፤ አንተም መቀበል ይገባሃል፤

5 ከዚያም አልፈህ የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ወደሚገኝበት ጊብዓ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደ ከተማይቱም መግቢያ በር በምትደርስበትም ጊዜ በኮረብታው ላይ መሥዋዕት አቅርበው የሚመለሱ የነቢያትን ጉባኤ ታገኛለህ፤ እነርሱም በገና እየደረደሩ፥ ከበሮ እየመቱ፥ ዋሽንት እየነፉ፥ በመሰንቆ ዜማ ሲዘምሩና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ትንቢት ሲናገሩ ታገኛቸዋለህ።

6 በድንገት የእግዚአብሔር መንፈስ በአንተ ላይ በኀይል ይወርዳል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት መናገር ትጀምራለህ፤ ልዩ ሰውም ትሆናለህ፤

7 እነዚህም ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ ማድረግ የሚገባህን ሁሉ አድርግ፤

8 የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕት ለማቅረብ አንተን ወደማገኝበት ወደ ጌልጌላ ቀድመኸኝ ትሄዳለህ፤ እኔ መጥቼ ምን ማድረግ እንደሚገባህ እስክነግርህ ድረስ ለሰባት ቀን በዚያው ቈይ።”

9 ሳኦልም ከሳሙኤል ተለይቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር ሳኦልን ሌላ አዲስ ሰው አደረገው፤ ሳሙኤል በምልክት የነገረውም ሁሉ በዚያን ቀን ተፈጸመ።

10 ሳኦል ወደ ጊብዓ በደረሰ ጊዜ የነቢያት ጉባኤ ከሳኦል ጋር ተገናኘ፤ በድንገት የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ላይ ወረደ፤ በዚያን ጊዜም እርሱ ከእነርሱ ጋር ትንቢት መናገር ጀመረ።

11 ከዚያ በፊት እርሱን የሚያውቁትም ሰዎች ይህን ሲያደርግ በተመለከቱ ጊዜ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።

12 በዚያም የሚኖር አንድ ሰው “የእነዚህስ የሌሎቹ ነቢያት ሁኔታ እንዴት ነው? አባቶቻቸውስ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል የምሳሌ አነጋገር የመነጨውም ከዚህ ነው።

13 ሳኦልም ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው መሠዊያ ወጣ።

14 የሳኦል አጐት ሳኦልንና አገልጋዩን አይቶ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ሳኦልም “አህዮች ልንፈልግ ሄደን ልናገኛቸው ስላልቻልን ሳሙኤልን ለመጠየቅ ጎራ ብለን ነበር” ሲል መለሰለት።

15 አጐትየውም “ሳሙኤል የነገረህን ንገረኝ” አለው።

16 ሳኦልም “የአህዮቹን መገኘት ነግሮናል” ሲል መለሰለት፤ ነገር ግን ንጉሥ ስለ መሆኑ ሳሙኤል የነገረውን ሁሉ ለአጐቱ አላወራለትም።


የሳኦል ንጉሥ መሆን በይፋ መነገሩ

17 ሳሙኤል ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ወደ ምጽጳ ጠራ።

18 እንዲህም አላቸው፦ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፦ ‘እናንተን እስራኤልን ከግብጽ አወጣኋችሁ፤ ከግብጽ ኀይልና ከሚጨቊኑአችሁ መንግሥታት ሁሉ ጭቈና አዳንኳችሁ’

19 ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቀታችሁ ያዳናችሁን አምላካችሁን ትታችኋል፤ እናንተም፦ ‘አይሆንም ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁት። አላችሁት። ስለዚህ አሁን በየነገዳችሁና በየወገናችሁ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ”።

20 ከዚህ በኋላ ሳሙኤል እያንዳንዱ ነገድ ወደ ፊት እንዲቀርብ አደረገ፤ የብንያምም ነገድ በዕጣ ተመረጠ፤

21 እንደገናም ሳሙኤል፥ የብንያም ነገድ ቤተሰቦች ሁሉ ወደፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከነዚያም የማጥሪ ቤተሰብ በዕጣ ተመረጠ፤ በመጨረሻም የማጥሪ ቤተሰብ ወንዶች ወደፊት እንዲቀርቡ አደረገ፤ ከእነርሱም መካከል ለቂስ ልጅ ለሳኦል ዕጣ ወጣ፤ እነርሱም በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙት አልቻሉም፤

22 ስለዚህም እነርሱ “ሌላ የቀረ ይኖር ይሆን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም “ሳኦል እነሆ በዕቃ መካከል ተደብቆ ይገኛል” ሲል መለሰላቸው።

23 ስለዚህም እነርሱ ፈጠን ብለው በመሄድ ከተሸሸገበት አውጥተው ወደ ሕዝቡ አመጡት፤ ሕዝቡም ሳኦል በትከሻውና በቁመት ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ተመለከቱ፤

24 ሳሙኤልም ሕዝቡን “እግዚአብሔር የመረጠው ሰው እነሆ ይህ ነው! ከእኛም መካከል እርሱን የሚስተካከለው የለም” አለ። ሕዝቡም ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ረጅም ዕድሜ ለንጉሡ ይሁን!” አሉ።

25 ሳሙኤልም ለሕዝቡ፥ ለአንድ ንጉሥ ሊደረግለት የሚገባውን ሥርዓት አስረዳቸው፤ ያንንም በመጽሐፍ ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት አስቀመጠው፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡን ሁሉ ወደየቤቱ አሰናበተ፤

26 ሳኦልም በጊብዓ ወደሚገኘው ቤቱ ተመልሶ ሄደ፤ እግዚአብሔር ልባቸውን ያነሣሣው ኀያላንም ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤

27 ነገር ግን አንዳንድ ሥርዓተ አልባዎች “አሁን ይህ ሰው እኛን ለማዳን ይችላል?” ተባባሉ፤ እርሱንም በመናቅ ምንም ዐይነት ገጸ በረከት ሳያመጡለት ቀሩ። ሳኦል ግን ዝም አለ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos