ዘፍጥረት 21:21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናቱም ከአንዲት ግብጻዊት ጋር አጋባችው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብጽ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፥ እናቱም ከምድረ ግብጽ ሚስት ወሰደችለት። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት። |
ስለዚህ ሣራይ ግብጻዊት የሆነች አገልጋይዋን አጋርን ለአብራም ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው። ይህም የሆነው አብራም በከነዓን ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ነው።
የእስማኤል ዘሮች ከግብጽ በስተምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ይኖሩ ነበር፤ የኖሩትም ከሌሎቹ የአብርሃም ዘሮች ጋር በጥላቻ ተራርቀው ነበር።
ርብቃ ይስሐቅን “ዔሳው ባገባቸው በእነዚህ በሒታውያን ሴቶች ምክንያት መኖሬን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ደግሞ ከነዚህ ከሒታውያን ሴቶች አንዲቱን ካገባ ከመኖር ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።
እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ በዚያም ጥቂቶች ሰዎች ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ግብጽ ተጒዘው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም ለሀዳድ መሬትና አንድ መኖሪያ ቤት ሰጥቶ ምግብ ፈቀደለት፤
እግዚአብሔር በቅድስናው ከቴማን አገርና፥ ከፋራን ተራራ እንደገና ይመጣል፤ መለኮታዊ ክብሩ ሰማያትን ሸፍኖአል፤ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል።
በፋራን ምድረ በዳ በቃዴስ ወደነበሩት ወደ ሙሴና አሮን ወደ መላውም የእስራኤል ማኅበር መጡ፤ እነርሱም ያዩትን ነገር ሁሉ አስረዱ፤ ያመጡትንም ፍሬ አሳዩአቸው፤
ወደ ቤቱም ተመልሶ ለአባቱና ለእናቱ “በቲምና ከፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አንድዋን አይቼ ወድጃታለሁ፤ ስለዚህ እርስዋን አጭታችሁ አጋቡኝ” አላቸው።
ሳሙኤል ሞተ፤ መላው እስራኤላውያንም በአንድነት መጥተው አለቀሱለት፤ ከዚያም በኋላ በራማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቀበሩት። ከዚያም በኋላ ዳዊት ወደ ፋራን ምድረ በዳ ሄደ፤