Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ማርያምና አሮን ሙሴን እንደ ተቃወሙ

1 ሙሴ ከኩሽ ነገድ የሆነች (ኢትዮጵያዊት) ሴት በማግባቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በሐሜት እንዲህ ሲሉ ነቀፉት፦

2 “እግዚአብሔር የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አማካይነት ተናግሮ የለምን?” እግዚአብሔርም እነርሱ የተናገሩትን ሁሉ ሰማ።

3 (በመሠረቱ ሙሴ በምድር ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ትሑት ሰው ነበር።)

4 በድንገትም እግዚአብሔር ሙሴን፥ አሮንንና ማርያምን “እናንተ ሦስታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን ኑ!” አላቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤

5 እግዚአብሔርም በደመና ዐምድ ወርዶ በድንኳኑ ደጃፍ በመቆም “አሮን! ማርያም!” ብሎ ጠራቸው፤ ሁለቱም ወደ ፊት ቀረቡ፤

6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ እኔ የምነግራችሁን አድምጡ! በመካከላችሁ ነቢያት ቢኖሩ ራሴን የምገልጥላቸው በራእይ ነው፤ በሕልምም አነጋግራቸዋለሁ፤

7 ከአገልጋዬ ከሙሴ ጋር የምነጋገረው ግን እንደዚያ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው፤

8 ስለዚህም እኔ ከእርሱ ጋር ቃል ለቃል በግልጥ እነጋገራለሁ እንጂ ስውር በሆነ አነጋገር አልናገረውም፤ የእኔን የእግዚአብሔርን መልክ ያያል፤ ታዲያ፥ እናንተ በአገልጋዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ እንዴት ደፈራችሁ?”

9 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቈጥቶ ሄደ።

10 ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተነሣ፤ ጊዜ ማርያም ለምጻም ሆነች፤ ለምጹም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ፤ አሮን ወደ ማርያም በተመለከተ ጊዜ ለምጻም ሆና አያት።

11 አሮንም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ሆይ፥ በስንፍናችን ስለ ሠራነው ኃጢአት ይህ አሠቃቂ ቅጣት እንዲፈጸምብን አታድርግ፤

12 እርስዋንም በእናቱ ማሕፀን ሳለ ሞቶ ግማሽ አካሉ ከተበላ በኋላ እንደ ተወለደ ጭንጋፍ እንድትመስል አታድርግ።”

13 ስለዚህ ሙሴ “እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ ፈውሳት” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

14 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ላይ ቢተፋባት እንኳ ኀፍረትዋን ተሸክማ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ትቈይ የለምን? ስለዚህም እርስዋ ከሰፈር ወጥታ እስከ ሰባት ቀን ድረስ በገለልተኛ ቦታ ትቈይ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሳ ወደ ሰፈር ልትገባ ትችላለች።”

15 ከዚያም በኋላ ማርያም ከሰፈር ወጥታ ለብቻዋ ተዘግቶባት ቈየች፤ እርስዋ እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ ከሰፈር አልተንቀሳቀሱም።

16 ከዚያም በኋላ ከሐጼሮት ተነሥተው በፋራን ምድረ በዳ ሰፈሩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos