Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሳሙኤል መሞት

1 ሳሙኤል ሞተ፤ መላው እስራኤላውያንም በአንድነት መጥተው አለቀሱለት፤ ከዚያም በኋላ በራማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቀበሩት። ከዚያም በኋላ ዳዊት ወደ ፋራን ምድረ በዳ ሄደ፤


ዳዊትና አቢጌል

2-3 በዚያም ቤተሰቡ ከካሌብ ጐሣ የሆነ ናባል ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም የማዖን ተወላጅ ሲሆን በቀርሜሎስ ከተማ አጠገብ የእርሻ መሬት ነበረው፤ ታላቅ ባለጸጋ ከመሆኑም የተነሣ ሦስት ሺህ በጎችና አንድ ሺህ ፍየሎች ነበሩት፤ ሚስቱ አቢጌልም እጅግ የተዋበች አስተዋይ ሴት ስትሆን እርሱ ግን መልካም ጠባይ የጐደለው ባለጌ ሰው ነበር። ናባል በቀርሜሎስ በጎቹን ያሸልት ነበር፤

4 ዳዊትም በበረሓ ሳለ ይህንኑ ወሬ ሰማ፤

5 ስለዚህም ዐሥር መልእክተኞችን መርጦ ወደ ቀርሜሎስ እንዲሄዱና ናባልን አግኝተው የእርሱን ሰላምታ እንዲያቀርቡለት አዘዛቸው፤

6 ለናባልም ይነግሩት ዘንድ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፦ “ሰላም ላንተ፥ ሰላም ለቤትህ፥ ሰላም ያንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን ብላችሁ ሰላምታ አቅርቡለት።

7 በጎችህንም እንደምታሸልት ሰምቶአል፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜም ሁሉ ምንም ዐይነት ጒዳት እንዳላደረስንባቸው እንድታውቅ ይፈልጋል፤ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ከመንጋቸው አንድ እንኳ አልተወሰደባቸውም፤

8 እነርሱንም ብትጠይቃቸው ይህንኑ ይነግሩሃል፤ እነሆ ዛሬ እኛ የደስታ ግብዣ በሚደረግበት ቀን መጥተናል፤ እኛንም በመልካም ሁኔታ ትቀበለን ዘንድ ዳዊት ጠይቆአል፤ ስለዚህ ለእኛ ለአገልጋዮችህና ለወዳጅህ ለዳዊት ስትል የሚቻልህን ስጦታ አድርግልን።”

9 የዳዊት ሰዎችም ይህንኑ መልእክት በዳዊት ስም ለናባል አስረክበው ይጠባበቁ ጀመር፤

10 ናባልም በመጨረሻ “ኧረ ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? እኔ ስለ እርሱ ሰምቼም አላውቅም! እነሆ፥ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ከጌቶቻቸው በኰበለሉ አገልጋዮች ተሞልታለች!

11 ስለዚህ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም ለበጎች ሸላቾቼ ያረድኳቸውን እንስሶች አንሥቼ ከወዴት እንደ መጡ ለማላውቃቸው ሰዎች የምሰጥበት ምክንያት የለም!” አለ።

12 መልእክተኞቹም ተመልሰው መጥተው ናባል ያለውን ሁሉ ለዳዊት ነገሩት፤

13 ዳዊትም “በሉ ሰይፋችሁን ታጠቁ!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ፤ ዳዊትም ራሱ ሰይፉን ታጠቀ፤ ጓዝ የሚጠብቁ ሁለት መቶ ሰዎች ወደ ኋላ ትቶ አራት መቶ ሰዎች በማስከተል ገሥግሦ ለመሄድ ተነሣ።

14 ከናባል አገልጋዮች አንዱም የናባልን ሚስት አቢጌልን እንዲህ አላት፤ “ዳዊት ካለበት በረሓ መልእክተኞችን ከሰላምታ ጋር ወደ ጌታችን ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው፤

15 እነርሱ ግን ለእኛ በጎ አድራጊዎች ነበሩ፤ ምንም ችግር አልፈጠሩብንም፤ ከእነርሱ ጋር በዱር በነበርንበት ጊዜ ሁሉ ከእንስሶቻችን አንድ እንኳ ተሰርቆብን አያውቅም፤

16 መንጋዎቻችንን እየጠበቅን በቈየንበት ጊዜ ሁሉ በቀንም ሆነ በሌሊት እነርሱ ለእኛ አጥር ሆነውን ነበር።

17 እባክሽን ይህን ጉዳይ አስቢበትና ማድረግ ስለሚገባሽ ነገር ወስኚ፤ አለበለዚያ ለጌታችንና ለቤተሰቡ ሁሉ አደገኛ ጥፋት ይሆናል፤ እርሱ እንደ ሆነ የማንንም ምክር የማይሰማ ደረቅ ሰው ነው!”

18 አቢጌልም በፍጥነት ሁለት መቶ እንጀራ፥ ወይን ጠጅ የተሞላበት ሁለት የወይን አቁማዳ፥ አምስት የተጠበሱ በጎች፥ ዐሥራ ሰባት ኪሎ የተጠበሰ እሸት፥ አንድ መቶ ዘለላ ወይንና ሁለት መቶ የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ በአንድነት ሰብስባ በአህዮች ላይ ጫነች።

19 ከዚህም በኋላ አገልጋዮቹን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋላሁ” አለቻቸው፤ ለባልዋ ግን የነገረችው ቃል አልነበረም።

20 እርስዋም በአህያ ላይ ተቀምጣ እየጋለበች በኮረብታው ጥግ በሚገኘው ጠመዝማዛ መንገድ ስትወርድ በድንገት ዳዊትና ተከታዮቹ ወደ እርስዋ ሲመጡ አገኘቻቸው፤

21 ዳዊትም በልቡ እንዲህ እያለ ያስብ ነበር፤ “የዚያን የማይረባ ሰው ሀብት በዚህ በረሓ ለምን ስጠብቅ ቈየሁ? የእርሱ ከሆነው ንብረት ምንም ነገር ተሰርቆበት አያውቅም፤ ታዲያ እኔ ስላደረግሁለት መልካም ነገር እርሱ የሚከፍለኝ ወሮታ ይህ ሆኖ ቀረ!

22 ከመንጋቱ በፊት የእርሱ የሆኑትን ወንዶች ሁሉ አንድ እንኳ ሳላስቀር በሙሉ ሳልገድል ብቀር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!”

23 አቢጌልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ በፍጥነት ከአህያዋ ወርዳ በዳዊት ጫማ አጠገብ መሬት ላይ ለጥ ብላ እጅ ነሣች፤

24 በጫማውም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ! እባክህ የእኔን የአገልጋይህን ቃል አድምጠኝ! በደሉን እኔ ልሸከም፤

25 የናባልን ጉዳይ ከቁም ነገር አታግባው! እርሱ ልክ እንድ አስሙ አጠራር ሞኝ ነው! ጌታዬ፥ የአንተ አገልጋዮች በመጡ ጊዜ እኔ በዚያ አልነበርኩም፤

26 የበቀል እርምጃ በመውሰድ ጠላቶችህን እንዳትገድል የጠበቀህ ራሱ እግዚአብሔር ነው፤ እነሆ፥ እኔ አሁን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ጠላቶችህና አንተን ለመጒዳት የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤

27 ጌታዬ ሆይ! እባክህ ይህ እኔ አገልጋይህ ያመጣሁልህን ስጦታ ተቀብለህ ለአገልጋዮችህ ይሁን።

28 ጌታዬ፥ አንተ የእግዚአብሔርን ጦርነት እየተዋጋህ ነው፤ በምትኖርበትም ዘመን ሁሉ ምንም ዐይነት ክፉ ነገር ማድረግን ስለማትፈልግ ስለ ፈጸምኩት በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ እግዚአብሔር አንተንና ዘሮችህን ለዘለዓለም ያነግሣል፤

29 ማንም ሰው በአንተ ላይ አደጋ ጥሎ ሊገድልህ ቢፈልግ አንድ ሰው ውድ የሆነ ሀብቱን እንደሚጠብቅ አምላክህ እግዚአብሔር አንተን በሰላም ይጠብቅሃል፤ ስለ ጠላቶችህም የሆነ እንደ ሆነ አንድ ሰው ድንጋዩን ከወንጭፍ እንደሚያስፈነጥር እግዚአብሔር ራሱ አሽቀንጥሮ ይጥላቸዋል።

30 እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፥ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ባደረገልህና በእስራኤልም ላይ በሚያነግሥህ ጊዜ፥

31 ምንም ዐይነት ጸጸት ወይም የኅሊና ወቀሳ አይደርስብህም። ጌታዬ ሆይ፥ ያለ ምክንያት ወይም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ብለህ የገደልከው ሰው የለም፤ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር በሚባርክህ ጊዜ እኔንም አትርሳኝ።”

32 ዳዊትም እንዲህ አላት፤ “ከእኔ ጋር እንድትገናኚ አንቺን ወደ እኔ የላከ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን!

33 በዛሬው ቀን ደም ከማፍሰስና በቀልንም ከመበቀል የጠበቀኝ መልካም አስተሳሰብሽ የተባረከ ይሁን፤ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።

34 በአንቺ ላይ ጒዳት ከማድረስ እግዚአብሔር ጠብቆኛል፤ ፈጥነሽ ወደ እኔ ባትመጪ ኖሮ ግን፥ ከናባል ወንዶች አንድ እንኳ ሳላስተርፍ ከንጋት በፊት ሁሉንም ለመግደል በሕያው እግዚአብሔር ስም ምዬ ነበር።”

35 ከዚያም በኋላ ዳዊት ያመጣችለትን ስጦታ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ተመልሰሽ ሂጂ፤ ልመናሽን ሰምቼአለሁ፤ የጠየቅሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አላት።

36 አቢጌልም እንደ ቤተ መንግሥት ግብር ታላቅ ግብዣ በማድረግ ላይ ወደነበረው ወደ ናባል ተመልሳ ሄደች፤ እርሱም ሰክሮ በደስታ ይፈነድቅ ስለ ነበር እስከ ማግስቱ ጧት ድረስ ምንም ቃል አልነገረችውም፤

37 በማግስቱም ስካሩ ከበረደለት በኋላ ሁሉንም ነገር አስረዳችው፤ ልቡም በድንጋጤ ስለ ተመታ እንደ ድንጋይ ሆነ።

38 ከዐሥር ቀኖች በኋላም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ናባል ሞተ።

39 ዳዊትም የናባልን መሞት በሰማ ጊዜ “እኔን በመስደቡ እግዚአብሔር ናባልን ስለ ተበቀለውና እኔንም ከስሕተት ስለ ጠበቀኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እርሱ ናባልን ስለ ክፉ ሥራው ቀጥቶታል” አለ። ከዚህም በኋላ ዳዊት ወደ አቢጌል መልእክተኛ ልኮ ሊያገባት መፈለጉን ገለጠላት።

40 አገልጋዮቹም እርስዋ ወዳለችበት ወደ ቀርሜሎስ ሄደው “ሊያገባሽ ስለ ፈቀደ ወደ ዳዊት ልንወስድሽ መጥተናል” አሉአት።

41 አቢጌልም ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ በመንሣት “እኔ ለእርሱ ገረዱ ነኝ፤ የአገልጋዮቹንም እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” አለች።

42 ፈጥናም ተነሥታ በአህያዋ ላይ ተቀመጠች፤ በአምስት ገረዶችዋም ታጅባ ከዳዊት አገልጋዮች ጋር በመሄድ ሚስቱ ሆነች።

43 ዳዊት ከዚህ በፊት የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችውን አሒኖዓምን አግብቶ ነበር፤ አሁን ደግሞ አቢጌልን አገባ፤

44 ይህ በዚህ እንዳለ ሳኦል የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን የጋሊም ተወላጅ ለሆነው ለላዊሽ ልጅ ለፓልጢ ዳረለት።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos