ዘፍጥረት 1:26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችንና በአምሳያችን እንፍጠር፤ ሰዎችም በባሕር ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎች፥ በሰማይ በሚበርሩ ወፎች፥ በእንስሶችና በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ በሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች፥ እንዲሁም በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እግዚአብሔርም አለ፦ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፥ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አለ፥ “ሰውን በአርኣያችንና በአምሳላችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሣዎችንና የምድር አራዊትን፥ የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ይግዛ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም አለ፤ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን እንስሳትንና ምድርን ሁ፤ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። |
እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ እንስሶችንና ወፎችን ሁሉ ፈጠረ፤ ምን ዐይነት ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳም ለእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ያወጣለት ስም መጠሪያው ሆነ።
እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ አዳም ክፉንና ደግን በማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ወስዶ በመብላት ለዘለዓለም እንዲኖር አይገባውም።”
ሰማያትን የፈጠረው እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ለምድር ቅርጽ ሰጥቶ የሠራት፥ የመሠረታትም እርሱ ነው፤ የፈጠራትም መኖሪያ እንድትሆን ነው እንጂ፥ ቅርጽ የሌላትና ባዶ እንድትሆን አይደለም፤ እርሱ፦ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤
ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ማንን እልካለሁ? መልእክተኛ የሚሆንልንስ ማን ነው?” ሲል ሰማሁት፤ እኔም “እነሆ እኔ እሄዳለሁ! እኔን ላከኝ!” አልኩ።
እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ በሆነው በአገልጋዬ በናቡከደነፆር ሥልጣን ሥር እንዲገዙለት ያደረግኹ እኔ ነኝ፤ የምድር አራዊትም ሳይቀሩ ይገዙለታል።
እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤ የተወሰኑ ዘመኖችንና የሚኖሩባቸውንም ቦታዎች መደበላቸው።
እኛ ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት ሆነን በመስታዋት እንደሚታይ ዐይነት የጌታን ክብር እናንጸባርቃለን፤ እኛም መንፈስ የሆነውን የጌታን መልክ ለመምሰል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።
የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን የማያምኑትን ሰዎች ልብ አሳወረው፤ በዚህም በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል የሚያበራላቸውን ብርሃን እንዳያዩ አደረጋቸው።