መዝሙር 149 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 እግዚአብሔርን አመስግኑ! ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ! በምእመናን ጉባኤ አመስግኑት! 2 የእስራኤል ሕዝቦች በፈጣሪያችሁ ደስ ይበላቸው! የጽዮን ሕዝቦችም በንጉሣችሁ ሐሤት ያድርጉ! 3 በማሸብሸብ ስሙን ያመስግኑት፤ ከበሮ እየመቱና በገና እየደረደሩ ያመስግኑት። 4 እግዚአብሔር በሕዝቡ ደስ ይለዋል፤ ድል በማቀዳጀት ትሑታንን ያከብራቸዋል። 5 የእግዚአብሔር ሕዝቦች በድል አድራጊነታቸው ደስ ይበላቸው፤ ሌሊቱን በሙሉ በደስታ ይዘምሩ። 6 ስለ ታም ሰይፍ በእጆቻቸው ይዘው እልል እያሉ እግዚአብሔርን በከፍተኛ ድምፅ ያመስግኑት። 7 እንደዚህ ቢያደርጉ መንግሥታትን ለማሸነፍ፥ አሕዛብንም ለመቅጣት፥ 8 ንጉሦቻቸውን በሰንሰለት ለመያዝ፥ መኳንንቶቻቸውን በእግር ብረት ለማሰር፥ 9 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የደነገገውን በመፈጸም የእግዚአብሔር ሕዝቦች ድልን ይጐናጸፋሉ። እግዚአብሔር ይመስገን። |