ዘፍጥረት 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየባቢሎን ግንብ 1 በመጀመሪያ የዓለም ሕዝቦች መነጋገሪያ ቋንቋ አንድ ብቻ ነበር፤ 2 ሰዎች ከምሥራቅ ተነሥተው በተጓዙ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ፤ በዚያም ተቀመጡ። 3 እርስ በርሳቸውም “ኑ! ጡብ እንሥራ፤ እንዲጠነክርም በእሳት እንተኲሰው” ተባባሉ፤ በዚህ ዐይነት የሚገነቡትን ጡብ አገኙ፤ በአንድነት የሚያጣብቁበትንም ቅጥራን አገኙ። 4 እንዲህም አሉ፦ “ኑ አንድ ከተማ እንመሥርት፤ በዚያም ጫፉ እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ እንዳንበታተን ስማችንን እናስጠራ።” 5 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሰዎቹ ይሠሩአቸው የነበሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ፤ 6 እንዲህም አለ፤ “እነሆ፥ እነዚህ ሰዎች አንድ ወገን ናቸው፤ መነጋገሪያ ቋንቋቸውም አንድ ነው፤ ይህም ከሚሠሩት የመጀመሪያው ብቻ ነው፤ በዚህ ዐይነት ሊሠሩ ያቀዱትን ሁሉ ማድረግ አያቅታቸውም። 7 ስለዚህ ኑ! እንውረድና እርስ በርሳቸው እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደበላልቀው።” 8 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማውንም መሥራት አቆሙ፤ 9 በዚያ እግዚአብሔር የሕዝቡን ቋንቋ ስለ ደበላለቀና እነርሱን በዓለም ዙሪያ ስለ በተናቸው የከተማውም ስም “ባቢሎን” ተባለ። ከሴም እስከ አብርሃም ( 1ዜ.መ. 1፥24-27 ) 10 የሴም ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፦ ከጥፋት ውሃ በኋላ ሁለት ዓመት ቈይቶ ሴም 100 ዓመት በሆነው ጊዜ አርፋክስድ የተባለ ልጅ ወለደ፤ 11 አርፋክስድን ከወለደ በኋላ 500 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ። 12 አርፋክስድም 35 ዓመት ሲሆነው ሳላሕን ወለደ። 13 ከዚህ በኋላ 403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 14 ሳላሕ 30 ዓመት ሲሆነው ዔቦርን ወለደ፤ 15 ከዚህ በኋላ 403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችንና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 16 ዔቦር 34 ዓመት ሲሆነው ፋሌቅን ወለደ፤ 17 ከዚህ በኋላ 430 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 18 ፋሌቅ 30 ዓመት ሲሆነው ረዑን ወለደ፤ 19 ከዚህ በኋላ 209 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 20 ረዑ 32 ዓመት ሲሆነው ሰሩግን ወለደ፤ 21 ከዚህ በኋላ 207 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 22 ሰሩግ 30 ዓመት ሲሆነው ናኮርን ወለደ፤ 23 ከዚህ በኋላ 200 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችን ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 24 ናኮር 29 ዓመት ሲሆነው ታራን ወለደ፤ 25 ከዚህ በኋላ 119 ዓመት ኖረ፤ ሌሎችንም ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆችን ወለደ። 26 ታራ 70 ዓመት ከሆነው በኋላ አብራምን፥ ናኮርንና ሃራንን ወለደ። የታራ ዘሮች 27 የአብራም፥ የናኮርና የሃራን አባት የነበረው የታራ ዘሮች የሚከተሉት ናቸው፤ ሃራን ሎጥን ወለደ፤ 28 ሃራን አባቱ ታራ ገና በሕይወት ሳለ በተወለደባት ከተማ በኡር ሞተ፤ ኡር የምትገኘው በከለዳውያን ምድር ነበር። 29 አብራም ሣራይን አገባ፤ ናኮር ደግሞ ሚልካን አገባ፤ እርስዋም ዪስካንን የወለደ የሃራን ልጅ ናት። 30 ሣራይ መኻን በመሆንዋ ልጅ አልወለደችም ነበር። 31 ታራ ልጁን አብራምን፥ ከሃራን የተወለደውን የልጅ ልጁን ሎጥን፥ የአብራም ሚስት የሆነችውን ምራቱን ሣራይን ይዞ በባቢሎን የምትገኘውን የኡርን ከተማ በመተው ወደ ከነዓን ምድር ለመሄድ ተነሣ፤ ወደ ካራን ዘልቀው እዚያ ተቀመጡ። 32 ታራ 205 ዓመት ሲሆነው በካራን ሞተ። |