ገላትያ 1:7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህንንም ያልኩት ግራ የሚያጋቡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች ስላሉ ነው እንጂ ወንጌልማ በመሠረቱ አንድ ብቻ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሌላ ወንጌል ያለ አይምሰላችሁ፤ የሚያናውጡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንዶች አሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እርሱ ግን ሌላ አይደለም፤ የሚያውኳችሁ ከክርስቶስም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አሉ እንጂ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። |
የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከቶ አትናገሩ፤ የእግዚአብሔር ቃል እንዴት ሸክም ሊሆን ይችላል? እናንተ ግን የሠራዊት ጌታ የሕያው እግዚአብሔርን ቃል ታጣምማላችሁ።
ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የእግዚአብሔርን ምርጦች እንኳ ለማሳሳት ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያሳያሉ።
እኛ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ንግድ ዕቃ እንደሚቸረችሩት እንደ ብዙዎቹ አይደለንም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላኩ ቅን መልእክተኞች በክርስቶስ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት እንናገራለን።
ስውርና አሳፋሪ የሆነውን ነገር አስወግደናል፤ በተንኰልም አንሠራም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አንለውጥም፤ ይልቅስ እውነትን በይፋ እናሳያለን፤ ራሳችንንም ለሰው ሁሉ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ እናደርጋለን።
ነገር ግን በመካከላችን ሾልከው በስውር የገቡ አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች እንዲገረዝ ፈልገው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ለስለላ በመካከላችን ሠርገው የገቡት በኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ነጻነት ነጥቀው ወደ ባሪያነት ሊመልሱን አስበው ነው።
ሌሎች ሰዎች ስለ እናንተ በመጨነቅ ያስባሉ፤ ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርጉት ለመልካም አይደለም፤ የእነርሱ ፍላጎት እናንተ ከእኛ እንድትለዩና ለእነርሱ በትጋት እንድታስቡ ነው።
ወዳጆች ሆይ! በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ስለ ተነሡ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ይልቅስ መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሩ።
ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡን የማያምኑ ብዙ አሳሳቾች በዓለም ተነሥተዋል። እንዲህ ያለው ሰው አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።
የሚፈረድባቸው መሆኑ ከብዙ ጊዜ በፊት የተጻፈባቸው አንዳንድ ሰዎች ወደ እናንተ ሾልከው ገብተዋል፤ እነርሱ የአምላካችንን ጸጋ በስድነት የሚለውጡ እግዚአብሔርን የማያመልኩ ናቸው፤ እርሱ ብቻ ገዢአችንና ጌታችን የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስንም ይክዳሉ።
ታላቁም ዘንዶ ወደታች ተጣለ፤ እርሱ መላውን ዓለም የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው። እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ የእርሱም መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ተጣሉ።
በመጀመሪያው አውሬ ፊት እንዲያደርግ በተፈቀደለት ተአምራት ምክንያት በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ያስት ነበር፤ በሰይፍ ቈስሎ ለዳነው ለአውሬው ክብር ምስል እንዲሠሩም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ያዛቸዋል።
ነገር ግን አውሬው ተያዘ፤ ከእርሱም ጋር በፊቱ ብዙ ተአምራት ያደርግ የነበረው ሐሰተኛው ነቢይ ተያዘ፤ እርሱ የአውሬው ምልክት የነበረባቸውንና ለአውሬውም ምስል ይሰግዱ የነበሩትን ተአምራት እያደረገ ያስታቸው ነበር፤ እነዚህ ሁለቱ በዲን ወደሚቃጠለው የእሳት ባሕር ከነሕይወታቸው ተጣሉ።
ሥራህን፥ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ክፉዎችን ግን ልትታገሣቸው እንዳልቻልክ፥ ሐዋርያት ሳይሆኑም ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ።
ነገር ግን አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም ‘ነቢይት ነኝ’ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለህ ታግሠሃታል፤ እርስዋ አገልጋዮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በማስተማር አሳስታቸዋለች።
ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሕዝቦችን እንዳያስት መልአኩ ዘንዶውን ወደ ጥልቁ ጒድጓድ ጣለው፤ ዘግቶም በማኅተም አሸገው፤ ከዚያ በኋላ ለጥቂት ጊዜ መፈታት ይገባዋል።