Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ራእይ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


(1) የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን

1 ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ ሰባቱን ኮከቦች በቀኝ እጁ ከያዘውና በሰባቱ የወርቅ መቅረዞች መካከል ከሚመላለሰው የተነገረ ነው፤

2 ሥራህን፥ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ፤ ክፉዎችን ግን ልትታገሣቸው እንዳልቻልክ፥ ሐዋርያት ሳይሆኑም ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ።

3 በትዕግሥት መጽናትህንና ስለ ስሜም ሳትሰለች መከራ መቀበልህን ዐውቃለሁ፤

4 ነገር ግን አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል፤

5 ከምን ያኽል ከፍተኛ ቦታ ላይ መውደቅህን አስታውስ! ንስሓም ግባ! በመጀመሪያ ታደርገው የነበረውን ሥራህን አድርግ፤ ይህን ሁሉ ባታደርግ ግን ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ንስሓም ካልገባህ መቅረዝህን ከስፍራው አነሣዋለሁ።

6 ነገር ግን የሚያስመሰግንህ አንድ ነገር አለ፤ ይህም እኔ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃል።

7 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! ‘ድል ለሚነሣ በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ካለው ከሕይወት ዛፍ ፍሬ እንዲበላ አደርገዋለሁ።’


(2) የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን

8 “ለሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ የመጀመሪያና የመጨረሻ ከሆነው፥ ሞቶ ከነበረውና ሕያው ከሆነው የተነገረ ነው፤

9 መከራህንና ድኽነትህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ሀብታም ነህ፤ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉ፥ የሰይጣን ማኅበር የሆኑ፥ ስምህን እንዳጠፉት ዐውቃለሁ፤

10 ወደ ፊት የሚደርስብህን መከራ አትፍራ፤ እነሆ፥ እንድትፈተኑ ከእናንተ አንዳንዶቹን ዲያብሎስ ወደ እስር ቤት ያገባችኋል፤ ዐሥር ቀንም መከራ ትቀበላላችሁ፤ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ የሕይወት አክሊል እሰጥሃለሁ።

11 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! “ድል የሚነሣ በሁለተኛው ሞት አይጐዳም።”


(3) የጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን

12 “ለጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤ “ይህ፥ በሁለት በኩል ስለት ያለውን ሰይፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤

13 አንተ የሰይጣን ዙፋን ባለበት ስፍራ መኖርህን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ስሜን አጥብቀህ ይዘሃል፤ በእኔ ላይ ያለህን እምነት አልካድክም፤ ታማኝ ምስክሬ የነበረው አንቲጳስ ሰይጣን በሚኖርበት በእናንተ ከተማ በተገደለ ጊዜ እንኳ በእኔ ማመንህን አልተውክም።

14 ነገር ግን የምነቅፍብህ አንዳንድ ነገሮች አሉኝ፤ ይኸውም የበለዓምን ትምህርት የያዙ አንዳንድ ሰዎች በመካከላችሁ አሉ፤ ይህ በለዓም የእስራኤል ሕዝብ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ በመብላትና ዝሙት በማድረግ እንዲሰናከሉ ባላቅን የመከረ ነው።

15 እንዲሁም የኒቆላውያንን ትምህርት የያዙ ሰዎችም በመካከላችሁ አሉ፤

16 ስለዚህ ንስሓ ግባ፤ አለበለዚያ በቶሎ ወደ አንተ መጥቼ እንደ ሰይፍ ባለው ከአፌ በሚወጣው ቃል እዋጋቸዋለሁ።

17 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ! ድል ለሚነሣ ከተሰወረው መና እሰጠዋለሁ፤ አዲስ ስም የተጻፈበትን ነጭ ድንጋይም እሰጠዋለሁ፤ ከተቀባዩ በቀር ይህን ሌላ ማንም አያውቀውም።


(4) የትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን

18 “ለትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ “ይህ የእሳት ነበልባል የሚመስሉ ዐይኖች ካሉትና በእሳት ፍም የነጠረ ናስ የሚመስሉ እግሮች ካሉት፥ ከእግዚአብሔር ልጅ የተነገረ ነው፤

19 ሥራህንና ፍቅርህን፥ እምነትህንና አገልግሎትህን፥ በትዕግሥት መጽናትህንም ዐውቃለሁ፤ የኋለኛው ሥራህ ከፊተኛው እንደሚበልጥም ዐውቃለሁ።

20 ነገር ግን አንድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም ‘ነቢይት ነኝ’ የምትለዋን ሴት ኤልዛቤልን ችላ ብለህ ታግሠሃታል፤ እርስዋ አገልጋዮቼ እንዲሴስኑና ለጣዖት የተሠዋ ምግብ እንዲበሉ በማስተማር አሳስታቸዋለች።

21 ንስሓ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት፤ እርስዋ ግን ከዝሙትዋ ንስሓ መግባትን አልፈለገችም።

22 ስለዚህ በሥቃይ አልጋ ላይ እጥላታለሁ፤ ከእርስዋ ጋር ከሠሩት ከክፉ ሥራቸው ንስሓ ገብተው ካልተመለሱ በቀር ከእርስዋ ጋር ያመነዘሩትንም ሁሉ ብርቱ ሥቃይ አመጣባቸዋለሁ፤

23 ልጆችዋንም በሞት እቀጣለሁ፤ አብያተ ክርስቲያንም ሁሉ የሰውን ሐሳብና ምኞት የምመረምር እኔ መሆኔን ያውቃሉ፤ ለእያንዳንዳችሁም እንደየሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።

24 “በትያጥሮን ላላችሁትና ይህን መጥፎ ትምህርት ላልተቀበላችሁት ሁሉ፥ እንዲሁም አንዳንዶች ‘የሰይጣን ጥልቅ ምሥጢር ነው’ የሚሉትን ላልተከተላችሁ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፤

25 ሆኖም እኔ እስክመጣ ድረስ ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ።

26 ድል ለሚነሣ፥ በሥራዬም ላይ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በአሕዛብ ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤

27 ‘በብረትም በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ዕቃም ቀጥቅጦ ያደቃቸዋል፤’ ይህም ሥልጣን እኔ ከአባቴ እንደ ተቀበልኩት ዐይነት ነው፤

28 የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ።

29 “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos