ገላትያ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጳውሎስ ሹመትና ትምህርት 1 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና ከሙታን ለይቶ በአስነሣው በእግዚአብሔር አብ ነው እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ሐዋርያ ካልሆነ ከጳውሎስ፥ 2 አብረውኝ ካሉ ከወንድሞቻችንም፥ በገላትያ ላሉ አብያተ ክርስቲያን፤ 3 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን። 4 በክፉ ከሚቃወም ከዚህ ዓለም ያድነን ዘንድ በአባታችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን አሳልፎ ሰጠ። 5 ለእርሱ ክብር ይሁን፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም አሜን። 6 በጸጋዉ የጠራችሁን ክርስቶስን ከማመን ወደ ልዩ ወንጌል እንዴት ፈጥነው እንዳስወጧችሁ አደንቃለሁ። 7 እርሱ ግን ሌላ አይደለም፤ የሚያውኳችሁ ከክርስቶስም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አሉ እንጂ። 8 እናንተ ግን የእኛን ፍለጋ ተከተሉ፤ እናንተስ እኛም ብንሆን ወይም መልአክ ከሰማይ ወርዶ እኛ ካስተማርናችሁ ወንጌል ሌላ ቢሰብክላችሁ ውጉዝ ይሁን። 9 አስቀድሜ እንደ አልሁ አሁንም ደግሞ እላለሁ፦ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን። 10 አሁንስ ለእግዚአብሔር ያይደለ ለሰው ብዬ አስተምራለሁን? ወይስ ሰውን ደስ አሰኛለሁን? ሰውን ደስ ላሰኝ ብወድስ የክርስቶስ ባሪያ አይደለሁም። ቅዱስ ጳውሎስ ለሐዋርያነት እንደ ተጠራ 11 ወንድሞቻችን ሆይ፥ ያስተማርኋችሁ ወንጌል ስለ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ። 12 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ገለጠልኝ እንጂ፥ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም፤ አልተማርሁትምም። 13 በአይሁድ ሥርዐት ውስጥ በነበርሁ ጊዜ፥ የነበረውን የቀድሞ ሥራዬን ሰምታችኋል፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እጅግ አሳድድና መከራ አጸናባቸው ነበር። 14 ለአባቶች ሥርዐት እጅግ ቀናተኛ ነበርሁና በወገኖች ዘንድ ከጓደኞች ሁሉ በአይሁድ ዘንድ እጅግ ከበርሁ። 15 ከእናቴ ማኅፀን ለይቶ ያወጣኝ እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ በጸጋው ጠራኝ። 16 በስሙም ለአሕዛብ ወንጌልን አስተምር ዘንድ፥ በእጄም የልጁ ክብር ይታወቅ ዘንድ ልጁን ገለጠልኝ፤ ያንጊዜም ከሥጋዊና ከደማዊ ሰው ጋር አልተማከርሁም። 17 ከእኔ በፊት ወደ ነበሩት ወደ ሐዋርያትም ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወደ ዐረብ ሀገር ሄድሁ፤ ዳግመኛም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። መጀመሪያ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ መውጣቱ 18 ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ኬፋን ላየው ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ በእርሱ ዘንድም ዐሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ። 19 ነገር ግን የጌታችን ወንድም ያዕቆብን እንጂ ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 20 ስለምጽፍላችሁም ነገር እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። 21 ከዚህም በኋላ ወደ ሶርያና ወደ ቂልቅያ አውራጃ መጣሁ። 22 በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ሀገር ማኅበረ ክርስቲያን ፊቴን አያውቁም ነበር። 23 ነገር ግን “ቀድሞ ምእመናንን ያሳድድ የነበረው እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን የሃይማኖት ትምህርት ዛሬ ይሰብካል” ሲባል ወሬዬን ይሰሙ ነበር። 24 ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያመሰግኑት ነበር። |