Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ገላትያ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሰላምታ

1 ከሰዎች ወይም በሰው አማካኝነት ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስና እርሱንም ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥

2 ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤

3 ከእግዚአብሔር አብና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

4 እንደ አምላካችንና አባታችን ፈቃድ፥ ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ሊያድነን፥ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።

5 ለእርሱ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።


ወንጌል አንድ ነው

6 በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ሌላ ወንጌል እንዴት ፈጥናችሁ እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ።

7 ሌላ ወንጌል ያለ አይምሰላችሁ፤ የሚያናውጡአችሁና የክርስቶስንም ወንጌል ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንዶች አሉ።

8 ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም ከሰማይ የመጣ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።

9 ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።

10 አሁን ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሳምናለሁን? ወይስ ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? እስከ አሁን ሰውን ደስ የማሰኝ ብሆን ኖሮ የክርስቶስ ባርያ አልሆንም ነበር።


ጳውሎስ እንዴት ሐዋርያ እንደሆነ

11 ወንድሞች ሆይ! በእኔ የተሰበከላችሁ ወንጌል ከሰው እንዳልሆነ አስታውቃችኋለሁ፤

12 በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንጂ ከሰው አልተቀበልሁትም ወይም አልተማርሁትም።

13 የአይሁድ እምነት ተከታይ በነበርኩበት ጊዜ እንዴት እንደ ኖርኩ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመጠን በላይ አሳድድና አጠፋ እንደ ነበር ሰምታችኋል፤

14 ለአባቶች ወግ ከመጠን በላይ ቅናት ስለ ነበረኝ፥ በአይሁዳዊነት ወገኖቼ ከነበሩት እኩዮቼ ብዙዎችን እበልጥ ነበር።

15 ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በወደደ ጊዜ፥

16 በአሕዛብ መካከል ወንጌሉን እንድሰብክ፥ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤

17 ወይም ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወደ አረብ አገር ሄድሁ፤ እንደገና ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።

18 ከዚያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፥ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ተቀመጥሁ፤

19 ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በስተቀር ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም።

20 ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።

21 ከዚያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ መጣሁ።

22 በክርስቶስ ያሉ የይሁዳ ቤተ ክርስቲያን አባላት አያውቁኝም ነበር፤

23 ነገር ግን “ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረው፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤

24 በእኔም ምክንያት እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos