Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ጢሞቴዎስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የክርስቶስ ታማኝ ወታደር በመሆን መከራ መቀበል

1 እንግዲህ ልጄ ሆይ! በኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው ጸጋ በርታ።

2 በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የተማርከውን ትምህርት ሌሎችን ለማስተማር ችሎታ ላላቸውና ለታመኑ ሰዎች ዐደራ ስጥ።

3 አንተም የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ወታደር በመሆን ከእኔ ጋር መከራን ተቀበል።

4 በወታደርነት የሚያገለግል ሰው የጦር አዛዡን ለማስደሰት ዝግጁ መሆን አለበት እንጂ ወታደራዊ ባልሆነ ጉዳይ ላይ አይውልም።

5 እንዲሁም በሩጫ የሚወዳደር ሰው በደንቡ መሠረት ካልተወዳደረ የአሸናፊነት የድል አክሊልን ሽልማት አያገኝም።

6 በሥራ የሚደክም ገበሬ ከሥራው ከሚገኘው ፍሬ የመጀመሪያውን ማግኘት ይገባዋል።

7 ጌታ በሁሉ ነገር ማስተዋልን ስለሚሰጥህ እኔ የምለውን ልብ ብለህ አስብ።

8 ከሞት የተነሣውንና የዳዊት ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስታውስ፤ እኔም የማበሥረው ወንጌል ይኸው ነው።

9 በዚህም ወንጌል ምክንያት እንደ ወንጀለኛ በሰንሰለት ታስሬ መከራ እቀበላለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም።

10 ስለዚህ እነርሱም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚገኘውን መዳንና ዘለዓለማዊ ክብርን እንዲያገኙ እግዚአብሔር ለመረጣቸው ሰዎች ስል ሁሉን ነገር እታገሣለሁ።

11 እንዲህ የሚለው ቃል የታመነ ነው፦ “ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን።

12 በትዕግሥት ጸንተን ከተገኘን ከእርሱ ጋር እንነግሣለን። ከካድነው እርሱም ደግሞ ይክደናል።

13 እኛ ታማኞች ባንሆን እርሱ ግን ራሱን ስለማይክድ ሁልጊዜ ታማኝ ሆኖ ይኖራል፤”


ትጉህ ሠራተኛ

14 ይህን ነገር አስገንዝባቸው፤ በቃላት ምክንያት እንዳይከራከሩም በጌታ ፊት አስጠንቅቃቸው፤ ይህ የቃላት ክርክር የሚሰሙትን ሰዎች ያጠፋል እንጂ ለምንም አይጠቅምም።

15 የእውነትን ቃል በትክክል እንደሚያደርስና በሥራውም እንደማያፍር ሠራተኛ ሆነህ ራስህን በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብና ተቀባይነትን ለማግኘት ጥረት አድርግ።

16 ዓለማዊና ከንቱ ከሆነ ልፍለፋ ራቅ፤ እንዲህ ዐይነቱ ልፍለፋ ሰዎችን ይበልጥ ከእግዚአብሔር እንዲርቁ ያደርጋቸዋል፤

17 የእነርሱ ንግግር እንደማይድን ቊስል ይቦረብራል፤ ከእነርሱም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ።

18 እነዚህ ሰዎች “የሙታን ትንሣኤ ገና ዱሮ ሆኖአል” እያሉ በመከራከር ከእውነት ርቀዋል፤ የአንዳንዶችንም ሰዎች እምነት ያናውጣሉ።

19 ነገር ግን “ጌታ የራሱ የሆኑትን ያውቃል፤” እንዲሁም “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ጸንቶ ይኖራል።

20 በትልቅ ቤት ውስጥ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆኑ ከእንጨትና ከሸክላ የተሠሩ ዕቃዎችም ይገኛሉ፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ለተከበረ አገልግሎት፥ አንዳንዶቹም ክብር ለሌለው አገልግሎት ይውላሉ።

21 ከእነዚህ ክብር ከሌላቸው ነገሮች ተለይቶ ንጹሕ ሆኖ የሚኖር ሰው ለተከበረ አገልግሎት እንደሚውል ዕቃ ይሆናል፤ ለማንኛውም መልካም አገልግሎት የተዘጋጀ ለጌታው የተቀደሰና ጠቃሚ መገልገያ ይሆናል።

22 ከወጣትነት ክፉ ምኞት ሽሽ፤ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩ ሰዎች ጋር ሆነህ ጽድቅን፥ እምነትን፥ ፍቅርን፥ ሰላምን ተከታተል።

23 ጠብን እንደሚያመጣ ዐውቀህ ከሞኝነትና ከከንቱ ክርክር ራቅ።

24 የጌታ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነ ሰው በሁሉም ዘንድ ገር፥ የማስተማር ችሎታ ያለውና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት እንጂ መጣላት አይገባውም፤

25 እርሱ የሚቃወሙትን ሰዎች በገርነት የሚያርም መሆን አለበት፤ ምናልባትም እውነትን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ንስሓ የመግባትን ዕድል ይሰጣቸው ይሆናል።

26 በዚህ ዐይነት ወደ ልቡናቸው ተመልሰው ዲያብሎስ ፈቃዱን እንዲፈጽሙ እነርሱን ከያዘበት ወጥመድ ያመልጣሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos