ዘዳግም 6:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነዚህን ሕግጋት አድምጡ! ታዘዙላቸውም! ይህን ብታደርጉ ለቀድሞ አባቶቻችሁ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በማርና በወተት በበለጸገች በዚያች ለም ምድር ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንላችኋል፤ ትበዛላችሁም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንግዲህ እስራኤል ሆይ ስማ፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት፣ ማርና ወተት በምታፈስሰው ምድር መልካም እንዲሆንልህና እጅግ እንድትበዛ፣ ትእዛዙንም ትጠብቅ ዘንድ ጥንቃቄ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ! መልካም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ ጌታ እንደ ተናገረ፥ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር፥ እጅግ እንድትበዛ በጥንቃቄ ጠብቅ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እስራኤል ሆይ፥ ስማ፦ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ይሰጥህ ዘንድ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ እጅግ እንድትበዛ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ።” ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ያዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ ሁሉ ይህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እንግዲህ፥ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ መልካም እንዲሆንልህ፥ የአባቶችህም አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወተትና ማር በምታፈስሰው ምድር እጅግ እንድትበዛ፥ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ። |
ቀጥሎም እግዚአብሔር አብራምን ወደ ውጪ አወጣውና “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትን መቊጠር ትችል እንደሆን ሞክር፤ እንግዲህ የአንተም ዘሮች እንደዚህ ይበዛሉ” አለው።
በግፍ ጭቈና ከሚሠቃዩባት ከግብጽ ምድር አውጥቼ እነሆ ዛሬ፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገች ሰፊና ለም የሆነች ምድር ልሰጣቸው ቃል ገብቻለሁ።
እኔ የቀድሞ አባቶችህ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤” በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።
እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ።
ይኸውም ኃጢአተኞች መቶ ጊዜ ወንጀል ቢሠሩም ለረጅም ዘመን ይኖራሉ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያከብሩ ሁሉ ነገር እንደሚሰምርላቸው ዐውቃለሁ።
መልካም ቢሆንም ባይሆንም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ቃል እንታዘዛለን፤ ወደ እርሱ የምንልክህም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብናከብር ሁሉ ነገር የሚሳካልን በመሆኑ ነው።”
ነገር ግን እኔ አምላካቸው ስሆን እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑ ዘንድ ለእኔ መታዘዝ እንደሚገባቸው ብቻ ነገርኳቸው፤ ሁሉ ነገር እንዲከናወንላቸው ከፈለጉም እኔ በሰጠኋቸው ሥርዓት እንዲኖሩ አዘዝኳቸው።
ትእዛዞቹንም ብትጠብቁ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻችሁና ለዘሮቻቸው ሊሰጣቸው ቃል በገባላቸው በማርና በወተት በበለጸገችው፥ በዚያች ለምለም ምድር ለረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።
በሰማይ ካለው ቅዱስ መኖሪያህ ሆነህ ወደ ታች ተመልከት፤ ሕዝብህን እስራኤልንም ባርክ፤ ለቀድሞ አባቶቻችን በገባኸው ቃል መሠረት የሰጠኸንን በማርና በወተት የበለጸገችውን ለም ምድር ባርክ።’
የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እንደሚሰጥህ ቃል በገባልህ መሠረት ምድሪቱን ለመያዝ በተሻገርህ ጊዜ የዚህን ሕግ ቃሎች በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ፤
ለቀድሞ አባቶቻቸው በመሐላ ቃል ኪዳን በገባሁላቸው መሠረት በማርና በወተት ወደ በለጸገችው ምድር አስገባቸዋለሁ፤ በዚያም በልተው በጠገቡና በወፈሩ ጊዜ እኔን ይተዋሉ፤ ቃል ኪዳኔንም አፍርሰው ሌሎች አማልክትን ያመልካሉ።
እግዚአብሔር አምላካችሁ ለዘለዓለም እንድትኖሩባት በሚያወርሳችሁ ምድር ለረጅም ዘመን ትኖሩ ዘንድ ለእናንተና ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም እንዲሆንላቸው እኔ ዛሬ የማዛችሁን ሕጉንና ትእዛዞቹን ጠብቁ።”
እነርሱን በጥንቃቄ ጠብቁአቸው፤ ይህንንም ስታደርጉ በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ ምን ያኽል ብልሆችና አስተዋዮች መሆናችሁን ታሳያላችሁ። እነዚህም ሌሎች ሰዎች ስለ ደንቦቹ ሲሰሙ ይህ ትልቅ ሕዝብ በእውነት ብልኅና አስተዋይ ነው ይላሉ።