ዘዳግም 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበድንጋይ ላይ የተጻፉት የእግዚአብሔር ሕጎች 1 ከዚህም በኋላ ሙሴ ከእስራኤል መሪዎች ጋር ሆኖ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ዛሬ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ 2 የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ ታላላቅ የሆኑ ጥቂት ድንጋዮችን አቁመህ በኖራ ለስነው፤ 3 የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እንደሚሰጥህ ቃል በገባልህ መሠረት ምድሪቱን ለመያዝ በተሻገርህ ጊዜ የዚህን ሕግ ቃሎች በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ፤ 4 ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ እኔ ዛሬ ባዘዝኩህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በዔባል ተራራ ላይ አቁመህ በኖራ ለስናቸው፤ 5 በዚያም የብረት መሣሪያ ካልነካው ድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ 6 ለእግዚአብሔር ለአምላክህ የምትሠራው ማናቸውም መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ መሆን አለበት፤ በዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትህን አቅርብ። 7 የአንድነት መሥዋዕት አቅርበህ በዚያው እየተደሰትህ በእግዚአብሔር በአምላክህ ፊት ብላ። 8 በእነዚያም ድንጋዮች ላይ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሁሉ በግልጥ እንዲነበቡ አድርገህ ጻፍ።” 9 ሙሴም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ሆኖ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ ከልብ ሆነህ አድምጠኝ፤ እነሆ፥ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል፤ 10 ስለዚህም ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዞችና ድንጋጌዎች ሁሉ በመጠበቅ ለእኔ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ ሁን።” አለመታዘዝ የሚያስከትለው መርገም 11 በዚያን ቀን ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ 12 “ዮርዳኖስን ከተሻገራችሁ በኋላ ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ መቆም የሚገባቸው የስምዖን፥ የሌዊ፥ የይሁዳ፥ የይሳኮር፥ የዮሴፍና የብንያም ነገዶች ናቸው። 13 ለእርግማንም በዔባል ተራራ ላይ መቆም የሚገባቸው የሮቤል፥ የጋድ፥ የአሴር፥ የዛብሎን፥ የዳንና የንፍታሌም ነገዶች ናቸው። 14 ሌዋውያንም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከዚህ የሚከተለውን ቃላት ይናገሩ፦ 15 “ ‘እንጨት ጠርቦ፥ ድንጋይ አለዝቦ፥ ብረት አቅልጦ ጣዖት በመሥራት በስውር የሚሰግድለት ማንኛውም ሰው የተረገመ ይሁን! እግዚአብሔር የጣዖት አምልኮን ይጠላል።’ “ሕዝቡም ሁሉ ሲመልሱ ‘አሜን!’ ይበሉ። 16 “ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚያዋርድ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ” ይበሉ። 17 “ ‘የጐረቤቱን ድንበር የሚያፈርስ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 18 “ ‘ዕውርን ወደተሳሳተ አቅጣጫ የሚመራ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 19 “ ‘መብት በመግፈፍ መጻተኞችን፥ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆችንና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መበለቶችን የሚያንገላታ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 20 “ ‘የአባቱ ሚስቶች ከሆኑት ከየትኛዋም ጋር ግንኙነት በማድረግ የአባቱን ክብር የሚያዋርድ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 21 “ ‘ከእንስሳ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 22 “ ‘ከእኅቱ ወይም በአንድ በኩል ብቻ እኅቱ ከሆነች ሴት ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 23 “ ‘ከዐማቱ ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 24 “ ‘በሽምቅ ሰውን መትቶ የሚገድል ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 25 “ ‘በገንዘብ ተገዝቶ ንጹሑን ሰው የሚገድል ሁሉ የተረገመ ይሁን!’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። 26 “ ‘እነዚህን የእግዚአብሔርን ሕግ ቃላት ሁሉ የማይፈጽም ሁሉ የተረገመ ይሁን።’ “ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን’ ይበሉ። |