1 ዮሐንስ 5:6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ጥምቀቱን በሚያመለክት ውሃና ሞቱን በሚያመለክት ደም የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ የመጣው በውሃ ብቻ ሳይሆን በውሃና በደም ነው። ይህም እውነት ስለ ሆነ ይህ ነገር እውነት መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ይመሰክራል፤ አዲሱ መደበኛ ትርጒም በውሃና በደም የመጣው ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አልመጣም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፤ መንፈስ እውነት ነውና። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በውኃና በደም የመጣው ይህ ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በውኃው ብቻ አይደለም ነገር ግን በውኃና በደም ነው። የሚመሰክረውም መንፈሱ ነው፥ መንፈሱ እውነት ነውና። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም። |
የማንኛውም ሕያው ፍጥረት ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ ነው፤ ደሙ በመሠዊያው ላይ ለእናንተ ኃጢአት ማስተስረያ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ፤ ደምም ሕይወት ስለ ሆነ የኃጢአት ማስተስረያ ነው።
ይህም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም፤ እናንተ ግን፥ እርሱ ከእናንተ ጋር ስለ ሆነና በውስጣችሁም ስላለ ታውቁታላችሁ።
የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን ስላልሆነ እርሱ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይነግራችኋል።
ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።
ኢየሱስም “የእግዚአብሔርን ስጦታና ‘ውሃ አጠጪኝ!’ የሚልሽ ማን እንደ ሆነ ብታውቂው ኖሮ፥ እርሱን መለመን የሚገባሽ አንቺ ነበርሽ፤ እርሱም የሕይወትን ውሃ ይሰጥሽ ነበር” አላት።
እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ለዘለዓለም ከቶ አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውሃ፥ ለሚጠጣው ሰው ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውሃ ምንጭ ይሆናል።”
እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በደሙ የኃጢአታቸውን ስርየት እንዲያገኙ ነው፤ እግዚአብሔር ይህን ማድረጉ በትዕግሥቱ የቀድሞውን ኃጢአት እንዳልነበረ በማድረግ የራሱን ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ ነው።
የሃይማኖታችን ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር፦ “ሰው ሆኖ ተገለጠ፤ እውነተኛነቱ በመንፈስ ታወቀ፥ ለመላእክት ታየ፥ ለሕዝቦች ሁሉ ተሰበከ፥ በዓለም ያሉ ሰዎች አመኑበት፥ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ” የሚል ነው።
እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን ራሱ በምሕረቱ አዳነን፤ ያዳነንም በአዲስ ልደት መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በተገኘው መታደስ ነው።
ታዲያ፥ የእግዚአብሔርን ልጅ የናቀ፥ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳን ደም ያረከሰ፥ የጸጋን መንፈስ የሰደበ፥ እንዴት ያለ የባሰ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል!
በዘለዓለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር የሌለበት መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናገለግል ኅሊናችንን ከሞተ ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!
ወደ ሁለተኛዋ ውስጠኛ ክፍል የሚገባው ግን የካህናቱ አለቃ ብቻ ነው፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ቀን ብቻ ነው፤ እርሱም ስለ ራሱ ኃጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኃጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም።
እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ በዐቀደው መሠረት ለተመረጣችሁት፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ለመታዘዝና በደሙ ተረጭታችሁ ለመንጻት በመንፈስ ቅዱስ ለተቀደሳችሁት፥ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።
ይህም ውሃ አሁን እናንተን የሚያድን የጥምቀት ምሳሌ ነው፤ ይህ ጥምቀት የሰውነትን ዕድፍ ማስወገድ ሳይሆን ንጹሕ ኅሊናን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ልመና ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንኖር እርስ በርሳችን አንድነት ይኖረናል። ደግሞም የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።
ፍቅር ማለት እንዲህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን ስለ ወደድነው ሳይሆን እርሱ ስለ ወደደንና ኃጢአታችንን እንዲደመስስ ልጁን ስለ ላከልን ነው።
አዲስ መዝሙርም እንዲህ እያሉ ዘመሩ፦ “በደምህ ከየነገዱ፥ ከየቋንቋው፥ ከየወገኑ፥ ከየሕዝቡ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ለመዋጀት፥ አንተ ስለ ታረድህ የብራናውን ጥቅል መጽሐፍ ለመውሰድና ማኅተሞቹን ለመክፈት የተገባህ ሆነሃል፤
እኔም “ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ” አልኩት። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል፤