ያዕቆብ 1:17 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መልካም ስጦታ ሁሉ፥ ፍጹምም በረከት ሁሉ፥ እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከላይ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከላይ፣ ከሰማይ ብርሃናት አባት ይወርዳሉ፤ በርሱ ዘንድ መለዋወጥ፣ ከመዞር የተነሣ የሚያርፍ ጥላም የለም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም መልካም ስጦታና ፍጹም በረከት ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህም የሚመጣው እንደ ጥላ መዘዋወር ወይም መለዋወጥ ከሌለበት ከብርሃን አባት ከእግዚአብሔር ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። |
ትእዛዝህንም ምስክርህንም ሥርዓትህንም እንዲጠብቅ፥ ይህንንም ነገር ሁሉ እንዲያደርግ ያዘጋጀሁለትንም ቤት እንዲሠራ ለልጄ ለሰሎሞን ፍጹም ልብ ስጠው።”
ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፥ በክፉዎች ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት ደጃፍ ላይ መቅረትን መረጥሁ።
ከዚያ በኋላ ጌታ የዘለዓለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽም ይሆናልና በቀን ብርሃንሽ ፀሐይ መሆኑ ይቀራል፤ የጨረቃም ብርሃን በሌሊት አያስፈልግሽም።
እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አኖረዋለሁ፤ አንተም ብቻህን እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ።
ጌታም በደመናው ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አኖረ፤ መንፈሱም በእነርሱ ላይ ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተናገሩም።
ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?
እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገርን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!
እንግዲያውስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው!”
አንተን እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልከውስ ምን አለህ? እንግዲህ የተቀበልክ ከሆንክ፥ እንዳልተቀበልክ የምትመካው ስለ ምንድነው?
በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት እንዲሰጥ ብርሃን በልባችን ውስጥ ያበራ፥ “በጨለማ ብርሃን ይብራ፤” ያለው እግዚአብሔር ነው።
በእርሱ የተጠራችሁበት ተስፋ ምን እንደሆን፥ ከቅዱሳንም ጋር የሚኖራችሁን የርስት ክብር ባለጠግነት ምንነት እንድታውቁ፥ የልቦናችሁ ዐይኖች እንዲበሩ፤
ዐይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰማይ በታች ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሰጣቸውን፥ ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም፥ የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ በመሳት እንዳትሰግዱላቸውና እንዳታመልኳቸው ተጠንቀቁ።
እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ እርሱን ከቶ ማንም አላየውም፤ ማንም ሊያየውም አይችልም፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።
ከላይ የሆነችው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፥ ደግ፥ እሺ ባይ፥ ምሕረትና መልካም ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።
ፍቅር በዚህ ነው፥ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን ነገር ግን እርሱ እንደ ወደደን እና ለኃጢአታችንም ማስተስሪያ እንዲሆን ልጁን ስለላከልን ነው።
ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፤ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘለዓለምም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ።